ብራድ ሼርማን የሚወክሏቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ጥያቄ ተቀብለው ሊያነጋግሩ ይገባል- የአሜሪካ ኮንግረስ እጩ ተወዳዳሪ አሪካ ሮድስ - ኢዜአ አማርኛ
ብራድ ሼርማን የሚወክሏቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ጥያቄ ተቀብለው ሊያነጋግሩ ይገባል- የአሜሪካ ኮንግረስ እጩ ተወዳዳሪ አሪካ ሮድስ

ሚያዝያ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ)“የኮንግረስ አባል ብራድ ሼርማን ከሚወክሏቸው ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ጥያቄ ተቀብለው ሊያነጋግሩ ይገባል”ስትል የአሜሪካ ኮንግረስ እጩ ተወዳዳሪ አሪካ ሮድስ ገለጸች።
በሕዝብ የተመረጡ ባለስልጣናት ውግንናቸው ለወከላቸው ማህበረሰብ እንጂ ለጥቂት አግባቢዎች(ሎቢስቶች) ሊሆን አይገባም ብለዋል።
የካሊፎርኒያ ግዛት የኮንግረስ አባል ብራድ ሼርማን ከግዛቱ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ያልሆኑት በሕወሓት ሰዎች ድጋፍ ስለሚደረግልዎት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ አዘል አስተያየት የአሜሪካ ኮንግረስ እጩ ተወዳዳሪ አሪካ ሮድስ በትዊተር ገጿ ላይ አስፍራለች።
በሕዝብ የተመረጡ ባለስልጣናት ውግንናቸው ለጥቂት ግለሰቦች ሳይሆን ለወከላቸው ማህበረሰብ ሊሆን እንደሚገባ ተናግራለች።
የአሜሪካ ኮንግረስ የካሊፎርኒያ አውራጃ 32 እጩ ተወዳዳሪ አሪካ ሮድስ ከአንድ ወር በፊት በካሊፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ጋር ባደረገችው ውይይት ሕወሓት ለዜጎች ሕይወት ቅድሚያ በመስጠት ወደ ትግራይ እርዳታ የሚደርስበት ዋና መስመር ላይ የሚያደርገውን ማስተጓጎል ማቆም እንዳለበት መግለጿ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ ግጭት ማቆም ውሳኔ ተገቢና የሚደነቅ እርምጃ እንደሆነም ተናግላች።“አሁንም ሆነ ወደፊት የኮንግረስ አባል ሆኜ ከተመረጥኩ በካሊፎርኒያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በመደገፍ ከጎናቸው እቆማለሁ” ነው ያለችው የኮንግረስ እጩዋ በውይይቷ ወቅት።
በካሊፎርኒያ ግዛት የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በሚያራምዱት አቋም ዙሪያ ለማነጋገር የሚያቀርቡትን ጥያቄ የኮንግረስ አባልና ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ ተባባሪ አርቃቂ ብራድ ሼርማን እንዲያናግሯችው የሚያቀርቡትን ጥያቄ ውድቅ እያደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያኑና ኤርትራውያኑ ከአንድ ወር በፊት የ’ኤች አር 6600’ እና የ'ኤስ 3199' ረቂቅ ሕጎች የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ከወር በፊት የብራድ ሼርማን ቢሮ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
የኮንግረስ አባሉን ለማነጋገር ፈቃደኛ ካልሆኑ መኖሪያ ቤታቸው ፊት ለፊት በመሄድ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ዳያስፖራዎቹ አመልክተዋል።
የ36 ዓመቷ አሪካ ሮድስ የካሊፎርኒያ አውራጃ 32 እየተባለ በሚጣው አካባቢ ወክላ የዴሞክራት ፓርቲን በመወከል የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ለመሆን በሕዳር ወር 2015 ዓ.ም በሚካሄደው ምርጫ ከሚወዳደሩ ሰባት እጩዎች መካከል አንዷ ናት።
በዚህ አውራጃ ከሚወዳደሩት እጩዎች መካከል ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ ተባባሪ አርቃቂ ብራድ ሼርማን ይገኙበታል።
በካሊፎርኒያ ግዛት የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን አሪካ ሮድስ የካሊፎርኒያ አውራጃ 32 የኮንግረስ ተወካይ እንድትሆን የገንዘብ ድጋፍና የማህበራዊ ትስስር ገጽ ዘመቻ እያደረጉ ይገኛሉ።
በአሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የተቋቋሙ የሲቪክ ተቋማትና የዳያስፖራ አደረጃጀቶች እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ በሚካሄደው የአጋማሽ ዓመት(ሚድ ተርም) ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ ስራ ላይ የሚሳተፉ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች በድምጽ የመቅጣት የዘመቻ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ለዚህም ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በሚገኙበት ግዛት በወጣው የመራጮች የምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ በስፋት በመመዝገብ የተጀመረውን ዘመቻ እንዲደግፉ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
እ.አ.አ በ2021 የቨርጂኒያ ግዛት ገዢ ምርጫ በትውልደ-ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ድምጽ ታግዘው የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩው ግሌን ያንግኪን የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩን ቴሪ ማካውሊፍን አሸንፈው የግዛት ገዢ ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።