ቀጥታ፡

በኃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመቀስቀስና የዜጎችን አብሮነት ለማደፍረስ የሚሰሩ አካላትን ሴራ ማክሸፍ ይገባል

ሚያዚያ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ ) በኃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመቀስቀስና የዜጎችን አብሮነት ለማደፍረስ የሚሰሩ አካላትን ሴራ ማክሸፍ ይገባል ሲሉ የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

የኃይማኖት መሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች ችግራቸውንም ደስታቸውንም በጋራ ተጋርተዋል ብለዋል።

አንዱ ለአንዱ መኖር፣ መደጋገፍና መተባበር የሁለቱም እምነቶች አስተምህሮ ያዛል የሚሉት የኃይማኖት አባቶቹ፤ ይህንንም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የአብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ተመራማሪ ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የበርካታ አኩሪ እሴቶች ባለቤት ናት።

በተለይም ደግሞ የኃይማኖት እኩልነት፣ አብሮነትና መቻቻልን የታደለች መሆኑኗንም ነው ያነሱት።

የክርስትናና የአስልምና እምነቶች ጥንታዊና ነባር ከመሆናቸውም ባሻገር የሁለቱም እምነት ተከታዮች  በእውነተኛ ፍቅርና መተሳሰብ ተጋምደው መዝለቃቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሁለቱ የእምነት ተከታዮች ከመቻቻል ባለፈ ያላቸውን ታሪካዊ አንድነትና ፍቅር የሚያመላክቱ በርካታ ማሳያዎች መኖሩንም ጭምር ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡላማ ምክር ቤት አባልና የሰላምና እርቅ ዘርፍ ኋላፊ ሼህ መሃመድ ሲራጅ በበኩላቸው በፈጣሪ የሚያምን ከሰው ልጅ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአውሬ ጋርም ይላመዳል ይላሉ።

የፈጣሪን ትእዛዝ የማያከብር ሰው በፈጣሪ ዘንድ ቅጣቱ የከፋ ይሆናል የሚሉት ሼህ መሃመድ ይህንን በመፍራት ሁሉም አማኝ ኅብረተሰብ በጎ ነገር በመፈጸም መጽናት እንዳለበት መክረዋል።  

የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን መጠበቅ ለዘመናት የቆየና ለዚህም ብዙ መስዋዕትነትን የከፈለ ታላቅ ሕዝብ መሆኑን አንስተው ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።  

በኢትዮጵያ ያሉ የሁለቱ እምነት ተከታዮችም በአገር ላይ የመጣን አስከፊ ችግር በጋራ ከመጋፈጥ ባሻገር ተጋብተውና ተዋልደው የሚኖሩ ለዓለም ምሳሌ የሆኑ ሕዘቦች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።  

እንደ ቀሲስ ሠለሞን ገለጸ፤ ሃገርን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የሰከነ፣ የተረጋጋ ስብእና ሊኖረው ይገባል፤ ወጣቱ በስሜት እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ አለበት።

የእምነቱ ተከታዮችም የኃይማኖት አባቶችን ቃልና ትእዛዝ ብቻ መከተልና ማክበር የሚገባቸው ሲሆን በራስ ፍላጎትና ስሜት ላይ ብቻ መመርኮዝ አስተምሮው እንደማይፈቅድም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት አገር ለማፍረስና ሕዘቦችን ለማጋጨት ውጥን የያዙ አካላት ዋነኛ መሳሪያቸው ማኅበራዊ ሚዲያ መሆኑን ገልጸው ወጣቱ የዚህ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ለዘመናት የቆየውን የሕዝቡን አንድነትና ለማጥፋት ታጥቀው የተነሱ ኃይሎች መኖራቸውን ሼህ መሃመድ ገልጸው ሕዝቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት።

አንድነትን በማጠናከር ለጥፋት የተሰለፉ ኋይሎችን ማሳፈር እንደሚገባ ጠቁመው ዜጎችም ባልተረጋገጠ አሉባልታ ለጥፋት መሰለፍ እንደሌለባቸውም መክረዋል።

ሕዝቡ በሐሰት መረጃዎች እንዳይዋከብ በተለይም የኃይማኖት አባቶች ሕዝቡን የማረጋጋትና ሠላም እንዲሰፍን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።     

ሕዝቡ ለዘመናት ይዞ የቆየውን አንድንትና አብሮነት እንዲያጠናክር የኃይማኖት አባቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም