በድሬዳዋ የኢድ አል ፈጥር በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ማድረጉን ፖሊስ አስታወቀ

133

ድሬዳዋ ሚያዝያ 22/2014(ኢዜአ).1ሺህ 443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የድሬዳዋ የፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የህዝብ ግንኙነትና የለውጥ ስራዎች ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከበር በፖሊስ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በረመዳን ፆም ወር  በየአደባባዩና ጎዳናዎች  የሁለቱ ኃይማኖት ተከታዮች የድሬዳዋ መገለጫ የሆኑት የህብረት፣ የአንድነት በጋራ ጉዳዮችን የመከወን መልካም ተግባራትን  እንዳፀኑት ሁሉ፤ እነዚህ ተግባራት በዓሉን በማሳመርና በማድመቅ ይደገማሉ ብለዋል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ተግባራት ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነቱን በብቃት ተወጥቷል፤ እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የኢድ አልፈጥር በዓልም  ታላቁ የኢድ መስገጃ በሚከበርበት ስፍራና በመላው ከተማዋ ፖሊስ ከኅብረተሰቡ፣ ከማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ያለ ፀጥታ ስጋት እንዲከበር እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በበዓሉ ዋዜማ ሆነ በበዓሉ ዕለት የተዛባና ችግር ለመፍጠር የሚሞከር አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች  ሲያጋጥሙት በአቅራቢያው ለሚገኘው የፀጥታ አካል እንዲያሳውቅ ኮማንደር ገመቹ አሳስበዋል፡፡

በመምሪያው የትራፊክ ክፍል ከ300 በላይ በጎ ፈቃደኛ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች ጋር በመቀናጀት  በበዓሉ ዕለት ለአቅመ ደካሞች የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን ጨምረው  ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም