የአውሮፓ ህብረት ከኢጋድ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ህብረት ከኢጋድ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገ
ሚያዚያ 22/2014/ኢዜአ/ የአውሮፓ ህብረት ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ጋር በመተባበር ሶስት አንቡላንሶችና አንድ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ ያለው ተሸከርካሪ ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገ፡፡
ድጋፉ የተደረገው በኢጋድ አስተባባሪነት ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ ገንዘብ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ድጋፉንም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተረክበዋል ።
ከድጋፉ በተጨማሪ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ፣የጅቡቲ ጤና ሚኒስቴር እና ኢጋድ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱም ለኢትዮ- ጅቡቲ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች የኮቪድ 19 ክትባት ተደራሽነትን ለማሻሻል የሚያስችል ነው ተብሏል።
በዚህም ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚመላለሱ ከ10 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች የኮቪድ 19 ክትባት የሚወስዱ ይሆናል፡፡
በተያያዘ ዜናም ኢጋድ፣ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲና ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ የሚያስችል የማህበረሰብ ተሳትፎ ጥናት በጋራ ለማከናወን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነት መርሃ ግብሩም በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮናልድ ኮቢያ ፣የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ፣ ጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የአፍሪካ ህብረት ተወካይ ወርቅነሽ መኮነን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።