ቀጥታ፡

ለኤርትራ ስደተኞች የተዘጋጀው መጠለያ ጣቢያ እውን ሆኖ በማየቴ ከልብ ተደስቻለሁ- የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር

ጎንደር ሚያዝያ 22/2014(ኢዜአ)''በዳባት ከተማ ለኤርትራ ስደተኞች የተዘጋጀው አዲሱ መጠለያ ጣቢያ እውን ሆኖ በማየቴ ከልብ ተደስቻለሁ' ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን የአፍሪካ ቀንድና ታላላቅ ሐይቆች ቀጠና ዳይሬክተር ክሎመንታይን ንኩየት ስላሚ አስታወቁ፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ከተማ የዓለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የልዑካን ቡድን ተጎብኝቷል፡፡

በዚህ ወቅት ዳይሬክተሯ ክሎመንታይን ንኩየት ስላሚ ለኢዜአ እንደተናገሩት በጅምር ላይ የሚገኘውን የስደተኞች መጠለያ ከኢትዮጵያ መንግስት፣ ከአጋር አካላትና ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ለማጠናከር ጥረት ይደረጋል፡፡

"ስደተኞቹ ኢትዮጵያ ቀድሞ በተጠለሉባቸው አካባቢዎች ለረዥም አመታት በሰላም ሲኖሩ ነበር" ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በአካባቢው በተፈጠረው የሰላም ችግር ሳቢያ ነባሩን መጠለያ ጣቢያ እንዲለቁ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

"የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በእንግዳ ተቀባይነት ባሕላቸው መሰረት አዲስ ቦታ አዘጋጅተው ስደተኞቹን ወደ ተሻለ ቦታ እንዲዛወሩ ማድረጋቸው አስደስቶኛል" ብለዋል፡፡

''አዲሱን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያን ማቋቋም ያስፈለገው አሸባሪው ህወሃት ከከፈተው ጦርነት ጋር በተያያዘ በትግራይ ይኖሩ የነበሩ የኤርትራ ስደተኞች በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት ነው'' ያሉት ደግሞ የስደትና ስደተኞች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ናቸው፡፡

በተለይ ህፃፅና ሽመልባ በተባሉ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖሩ የነበሩ ስደተኞች በአሸባሪው ቡድን ከፍተኛ እንግልት አጋጥሟቸው እንደነበር አስታውሰው፣ አዲሱ መጠለያ ጣቢያ እስካሁን 8ሺህ 140 ስደተኞችን ተቀብሎ  እያስተናገደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያው የመኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋምና መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመው በቀጣይም ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማሟላት ስራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ወደ አዲሱ ዓለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መምጣቱን የሚናገረው ወጣት እርሃስ  ነጋሲ "ሸሽተን ስንመጣ በረሃ ላይ በርካታ ወንድሞቻችንን በሞት አጥተናል" ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ ወደ ሆነው ዓለም ዋጭ ወደ ተባለው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መግባቱን ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ 24 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች  ከ900ሺህ በላይ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን ከስደተኞች መካከል በዋነኝነት የደቡብ ሱዳን፣ የሱዳን፣ የኤርትራና የሶማሊያ ስደተኞች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም