ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

ሚያዝያ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በቅርቡ አዲስ ከተሾሙት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላዉድ ጂቢዳር ጋር ተወያይተዋል ።

አቶ ደመቀ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተሻለ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸው፤ በትግራይ ክልል በከባድ ሁኔታ ውስጥም እርዳታ ለሚሹ ዜጎች እያደረገ ያለው ሰብአዊ እርዳታ የሚመሰገን ነው ብለዋል ።

አቶ ደመቀ አክለውም አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፤እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም ያሉ ድርጅቶች ደግሞ ሁሉን አቀፍ ተደራሽ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ በማድረግ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን ነው ያሉት።

በትግራይ ክልል እየሰጠው ካለው ሰብአዊ እርዳታ በተጨማሪ በአማራ እና በአፋር ክልልም እንዲሁም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሥራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

መንግሥት ያልተገደብ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ ያሳለፈውን ውሳኔ በማክበር የተሻለ ድጋፍ እንዲደረግ እየሰራ መሆኑን ያወሱት አቶ ደመቀ፤ የህወሓት ቡድን ግን አሁንም ሰብአዊ እርዳታውን ለማስተጓጎል እየሞከረ ነው ብለዋል ።

ዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላትም የቡድኑን አካሄድ ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር በበኩላቸው የመንግሥትን ቁርጠኝነት በማድነቅ በቀጣይም አብሮ ለመስራት በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከችግር ወጥታ ወደ ተሻለ መንገድ እና እድገት መስመር መግባት ከራሷም በላይ ለሌሎች ሀገራትም ትልቅ ሚና ስላለው ከመንግስት ጎን ሆነን ችግሩን ለማለፍ እንሰራለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የውስጥ መፈናቀል ካጋጠማቸው ዜጎቿ በተጨማሪ ከ9መቶ ሺህ በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኗን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል ።

የምግብ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ስንዴን በከፍተኛ መጠን የማምረት አቅም ያላት ሀገር በመሆኗ ለዚህ ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ለአቶ ደመቀ ገልጸውላቸዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ በድርቅ ወደ ተጎዱ አካባቢዎችም እንደሚያስፋፋ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላዉድ በኢትዮጵያ የስራ ቆይታቸዉ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸዉ አቶ ደመቀ ገልፀውላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም