ጥፋት በጥፋት የማይታረም መሆኑን በመገንዘብ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል -ጉባኤው - ኢዜአ አማርኛ
ጥፋት በጥፋት የማይታረም መሆኑን በመገንዘብ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል -ጉባኤው
ወላይታ ሶዶ፤ ሚያዚያ 21/2014 (ኢዜአ) ጥፋት በጥፋት የማይታረም በመሆኑ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ማበርከት እንዳለበት የደቡብ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ ።
የደቡብ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መጋቢ ተሰማ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት ጥፋት በጥፋት የማይታረም በመሆኑ ህዝቡ ሰላምና ልማት በማይፈልጉ ሃይሎች ተቀርጸው የሚሰጡ አጀንዳዎችን ሳይቀበል በሰከነ መንገድ መንቀሳቀስ አለበት።
"የጥፋት ሃይሎች ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው ግጭትና ውድመት ማስከተላቸው ሃይማኖታዊ አቋምና ይዘት የሌለው ነው" ብለዋል።
"እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ጉዳዮች እየገጠሙን በመሆኑ ቆም ብሎ ማየት የሚጠይቅ ነው" ያሉት መጋቢ ተሰማ በተለይ ወጣቱ ምክንያቱን ሳይረዳ ፈጥኖ ወደሌላ ጥፋት ከመሄድ መቆጠብና ስውር አጀንዳዎችን ሌለይ እንደሚገባ አመልክተዋል።
"ሰሞኑን በጎንደር ከተማ የተከሰተው አሳፋሪ ድርጊት በፍጹም ሊደገም የማይገባው በመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል" ብለዋል ።
ድርጊቱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት የሚደረጉ ሙከራዎች መኖራቸውን ጠቁመው አንድን ጥፋት በሌላ ጥፋት መፍትሔ መስጠት እንደማይቻል ተናግረዋል።
ከጥንት ጀምሮ በሁለቱ ሀይማኖቶች መካከል ያለው የመተሳሰርና የመከባበር እሴት ጠንካራ መሆኑን አመልክተው "ፅንፈኞች ይሄን ጠንካራ አንድነት ለማጠልሸት አቅደው እየሰሩ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል "ብለዋል።
"በመሆኑም ዓላማቸውን ከጅምሩ በመቅጨት በህዝቦች መካከል አላስፈላጊ ጥላቻ እንዳይፈጠር ለማድረግ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል" ሲሉ አክለዋል።
ህዝቡ ሁኔታውን ጠንቅቆ በመረዳትና ለፅንፈኞች ምቹ አጋጣሚ ባለመፍጠር ለዘላቂ ሰላምና አንድነት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የደቡብ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ህሩያን ገሪማ ጌታነህ በበኩላቸው ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ቀድሞ መከላከል ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ድርጊቱን አውግዘዋል።
የትኛውም ሀይማኖት አስተምህሮ ግጭትና መጠፋፋትን እንደማያስተምር ገልፀው "የሀይማኖት ካባ ለብሰው ግጭቱን ለማስፋትና ለማባባስ የሚደረጉ ጥረቶች ህብረተሰቡ ባለመቀበል ሊያሳፍራቸው ያስፈልጋል "ብለዋል።
ፍትህ የሚገኘው የተፈጠረውን ጥፋት በመድገም ሳይሆን ዓላማውን ተረድቶ የሰላም መንገድ መፈለግ ሲቻል መሆኑንም ተናግረዋል።
"ሀይማኖት በሀገርና በሰላም ነው የሚያምረው" ያሉት ሊቀ ህሩያን ገሪማ በተለይም የሃይማኖት አባቶችና አስተማሪዎች ግጭቶችን የመከላከል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።
የደቡብ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ኡስታዝ ሳዲቅ ወጌቦ በበኩላቸው "የተፈጠረው ችግር የማይጠበቅና አሳዛኝ ድርጊት ነው" ብለዋል።
ጥቂት ሰላም ጠል ግለሰቦች የአብሮነትና የመተባበር እሴቶችን እንዲያጠለሹ መፍቀድ አይገባም ብለዋል።
ግለሰቦች በተለያዩ መንገዶችና አጋጣሚዎች የሀገርና የህዝብ ሰላም ሊማደፍረስ ሲሰሩ መቆየታቸውን ማስታወስ እንደሚገባ አስታውሰዋል።
"የኢትዮጵያ ህዝብ በሃይማኖቱ ጉዳይ በመከባበርና በሌሎች ጉዳዮች በሙሉ በመረዳዳትና በመደጋገፍ እስከዛሬ የመጣ በመሆኑ ወደፊትም ይህንን ምሳሌያዊ ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት" ብለዋል።
"በተለያየ መንገድ ሀገሪቱን ወደ ቀውስ ለማስገባት ሞክረው በህዝቦቿ አንድነትና ፍቅር የተሸነፉ ጠላቶች አሁን ደግሞ ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ መነሳታቸውን መገንዘብና ዓላማቸውን ማክሸፍ ያስፈልጋል" ሲሉም አክለዋል።
በደቡብ ክልልም በተለያዩ አከባቢዎች የሚታዩ በሃይማኖት ሽፋን የሚፈጠሩ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑን ገልጸው ችግሩን በእንጭጩ ለማስቆም ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።
"በተለይ በሰላም ተቻችሎና ተደጋግፎ በመኖር የማያተርፍ ባለመኖሩ ህዝቡ ለጽንፈኞችና ለጥፋት ጋባዦች ዕድል መስጠት የለበትም" ብለዋል።
ጉባኤው በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች የሰላም አማራጮች ላይ አተኩሮ እንዲሰራ መልዕክት ማስተላለፉን አስረድተዋል ።
ሁሉም አማኝ አከባቢውን በንቃት በመጠበቅ ሰላሙን ማስጠበቅ እንዳለበት ጠቁመዋል።