ሚኒስቴሩ ለአፋር ክልል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ ለአፋር ክልል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ሰመራ ሚያዝያ 21/2014(ኢዜአ)የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ጉዳት ለደረሰባቸዉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ማጠናከሪያ ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ለክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ዛሬ አስረክበዋል።
ከድጋፉ 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ የተደረገ ሲሆን፣ ቀሪው በቁሳቁስ እንደተደረገ ርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በዓይነት ከተደረገው ድጋፍ መካከል የተለያዩ ማሽነሪዎችና የእጅ መሳሪያዎች እንደሚገኙበት ተመልክቷል።
አቶ አወል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አሸባሪው ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ ይዟቸዉ በነበሩ አካባቢዎች በተለይ በሰብዓዊ ፍጡራን ከፍተኛ ግፍ ፈጽሟል።
በክልሉ የቂልበቲ-ረሱ ዞንን ሳይጨምር በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ብቻ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በክልሉ የደረሰውን ውድመትና ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ ባደረገው ርብርብ ህብረተሰቡ ችግሩን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ባደረገው ድጋፍ የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት እገዛ እንደሚያደርግ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
ለድጋፉ በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው አሸባሪው ቡድን በፈጸመው ወረራ ውደመት ከደረሰባቸው መካከል የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በመተባበር ተቋማቱን በተሻለ ደረጃ አደራጅቶ ወደ ስራ ለማስገባት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።