ወጣቱ ግጭትን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ለማድረግ የሚጥሩ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆን በሰከነ መንገድ ሊጓዝ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ግጭትን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ለማድረግ የሚጥሩ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆን በሰከነ መንገድ ሊጓዝ ይገባል
ሚያዚያ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) ወጣቱ በግለሰቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን የሃይማኖት ግጭት በማስመሰል ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን በጥንቃቄ መጓዝ እንዳለበት ተገለፀ።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የፌዴራሊዝምና የብዝሃነት አስተዳደር የፖሊሲ ጥናት ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ጥላሁን ተፈራ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ግጭት ተፈጥሯዊና በየትኛውም ማህበረሰብ የሚከሰት ቢሆንም ኃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶች እየተባባሱ መጥተዋል።
ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ያነገቡ አካላት በግለሰቦች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶች መልካቸውን ቀይረው የሀይማኖትና የብሄር እንዲመስሉ በማድረግ በህብረተሰቡ መካከል ልዩነት ለመፍጠር ሲጥሩ ይስተዋላል ብለዋል።
የግል ጥቅማቸውን ብቻ የሚያሳድዱ ለህዝብ ግድ የሌላችው ወገኖችም ግጭቶችን አግዝፈውና ያልሆነን ነገር ፈጥረውም ጭምር በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት አገርና ህዝብን እየጎዱ መሆኑን ተናግረዋል።
የሺህ ዘመናት ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረችው በማህበራዊ እሴቶቿ መሰረትነት መሆኑን አውስተው ባለፉት ሶስት አስርታት እነዚህ እሴቶች እንዲሸረሸሩ ተደርገዋል ብለዋል።
ብዝሃነትን ከአገራዊ አንድነት ጋር አጣጥሞ መሄድ ሲቻል በከፋፍለህ ግዛ አስተሳሰብ በህዝቦች መካከል ልዩነት ለመፍጠር ሲሰራ እንደነበርም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲከመርባቸው የነበረውን ከፋፋይ አስተሳሰብ በመጣለና በህብረት በመቆም አገራቸውን ማጽናት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ተሰሚነት እንዳያድግ የሚፈልጉ አገራት ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ በማጣላትና ክፍተትን በማስፋት ማዳከምን እንደሚሹ መረዳት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ልዩነትን ወደጎን በመተው ኢትዮጵያ እንደአገር ታስፈልገናለች የሚል እሳቤ የሁሉም ዜጋ ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።
እርስ በርስ መደማመጥና አንዱ የአንዱን ስሜት መረዳት እንዳለበትና ወጣቱም በሰከነ መንገድ መጓዝ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ