መገናኛ ብዙሃን የዜጎችን የአመለካከትና ሃሳብ ብዝሃነትን ባከበረ መልኩ መስራት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የዜጎችን የአመለካከትና ሃሳብ ብዝሃነትን ባከበረ መልኩ መስራት አለባቸው
ሚያዝያ 21/2014 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን የዜጎችን የአመለካከትና ሃሳብ ብዝሃነትን ባከበረ መልኩ መስራት እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ ኢትዮጵያን የሚመጥን የሚዲያ ተቋም እንዲፈጠር ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን ማከናወን አለበት።
በዚህም መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ-ምግባር እንዲሁም የአመለካከት እና የሃሳብ ብዝሃነትን ባከበረ መልኩ መስራት እንዳለባቸው ነው ያነሱት፡፡
የዴሞክራሲ ባህልን የሚያጎለብት ሚዲያ ተቋም ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
የመገናኛ ብዙሃኑ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዲችሉ እና ገለልተኛ፣ ተዓማኒና ተደራሽ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድም ሰፊ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የመረጃ አሰባሰብና ስርጭትን በሚመለከትም የቁጥጥር ስራን ማጠናከር እና ተጠያቂነትንም ማስፈን እንደሚገባም አክለዋል።
የሃሰተኛ እና ሚዛናዊነት የጎደላቸው መረጃዎችን በመቆጣጠር ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ ሚዲያ ለማህበረሰቡ እድገት አይነተኛ መሳሪያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ነጻ፣ አሳታፊ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት የሚያስችል የሚዲያ ሪፎርም ማከናወኑን አንስተው፤ ይህም በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣኑ መገናኛ ብዙሃን ነጻነታቸውን ጠብቀውና ህግና ስርዓትን አክብረው እንዲሰሩ በማድረግ ረገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አሰራሮችን በፖሊሲና ህግ የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም መመሪያዎችን የማዘጋጀት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዚህም በአገር ሕልውና እና ሉአላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 እና ሌሎች ሕጎችን የሚጥሱ ዜናዎችና ፕሮግራሞችን አሰራጭተው የተገኙ መገናኛ ብዙሃንን ላይ እንደጥፋታቸው መጠን የእርምት እርምጃ መወሰዱንም ጠቁመዋል፡፡