የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ ነው
ሚያዝያ 21/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል ከያዛቸው አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ለቆ አለመውጣቱ ሰብዓዊ ድጋፍ የማጓጓዝ ስራው ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንቱ በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብትና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ተግባራት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም መንግስት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር መጋቢት 24 ቀን 2022 የግጭት ማቆም ውሳኔ ተግባራዊ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ይህን ተከትሎም መንግስት ሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እስካሁንም ባለው ሂደትም 146 የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መቀሌ መድረሳቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
በርካታ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ ለቆ አለመውጣቱን ገልጸው፤ ይህም ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ተደራሽ በማድረግ ረገድ ተጽእኖ እያደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሰብዓዊ ድጋፎችን እንዲያቀርብና የሽብር ቡድኑ ከያዛቸው አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ለቆ እንዲወጣ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ለቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ምዋይ ኪባኪ ሞት የሃዘን መግለጫ ማስተላለፍ፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በምርጫ በማሸነፋቸው የደስታ መግለጫ መላክ ኢትዮጵያ በሳምንቱ ካከናወነቻቸው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ውስጥ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ለተወሰኑ ዓመታት ሰርተው የነበሩት የማሊ አምባሳደር ባሳለፍነው ሳምንት ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን በዛሬው እለትም አስከሬናቸው ወደ አገራቸው እንደሚሸኝ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን ወክለው በማልታ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ዱባይ፣ ብራዚልና ስዊድን የተሾሙ አምባሳደሮች ሰሞኑ የሹመት ደብዳቤ ለአገራቱ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ የሚሸጡ መድሃኒቶች የተሻለ ጥራት እንዲኖራቸው ከሚሰራው የአፍሪካ መድሃኒት ኤጀንሲ ጋር ስምምነት መፈራረሟንም አውስተዋል።
በሌላ በኩል በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለስ ተግባር ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በዚህ ሳምንት ከ2 ሺህ 300 በላይ ዜጎች ተመልሰዋል።
በአጠቃላይ እስካሁን ከ15 ሺህ 300 በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ቃል አቀባዩ አብራርተዋል።
"ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት ጉዞ " መርሃ ግብር ምክንያት በማድረግ የተዘጋጁ ኤክስፖና ሌሎች ሁነቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
መሰል መርሃ ግብሮች የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን ከግምት በማስገባት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መጥተው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በዘላቂነት የሚሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት 9 ወራት የዓለም አቀፍ ጫናዎችን በመቋቋም የአገር ሉአላዊነትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተሻለ መፈጸሙን የእቅድ ክንውኑን በትላንትናው እለት ሲገመግም ማንሳቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም ክፍተቶችን በመሙላት በውጭ ግንኙነት በኩል መሰራት ያለባቸው ተግባራትን መለየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ተናግረዋል።