ቀጥታ፡

ኢዜአ ለአብርሆት ቤተ መፅሓፍት የሚያደረገውን መጽሓፍ የማሰባሰብ ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል

ሚያዝያ 21/2014 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለአብርሆት ቤተ መፅሓፍት የሚያደረገውን መጽሓፍ የማሰባሰብ ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል ።

የኢዜአ ለአብርሆት ቤተ መጽሓፍት ማጠናከሪያ ከሰራተኞቹና ከተለያዩ አካላት መጽሓፍት እያሰባሰበ ይገኛል።

አርቲስት ደበበ እሽቱ በዚሁ መነሻነት ካላቸው መጽሓፍት ላይ ለትውልድ መገንቢያ ይሆናሉ ያሏቸውን መጽሓፈት ለግሰዋል።

አርቲስት ደበበ 'የደም እምባ'፣ 'የባሩድ ባርሜል'ና 'ለሊቀመንበሩ የተጻፉ ደብዳቤዎች' የተሰኙ መጽሓፍትን ተርጉመዋል።

በተጨማሪም መጀመሪያ ኢትዮጵያ ስለገባው የካቶሊክ ቄስ ታሪክ እንዲሁም በእስር ቤት ቆይታቸው ስለታዘቡት ነገር በመፅሓፍ መልክ ሰንደዋል።

አርቲስቱ እንደሚሉት መጽሓፍት በየመደርደሪያው ከሚያረጁ ወደማያረጀው የእውቀት ቤት መጥተው ትውልድ መገንቢያ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም ተነበውም ይሁን ሳይነበቡ በየቤቱ በየመደርደሪያው ላይ የተከማቹ መጽሓፍት ለአብርሆት ቤተ መጽሓፍት ሊለገሱ ይገባል ይላሉ።

ይህ ሲሆን መጪው ትውልድ የተሻለ እውቀት ጨብጦ ራሱንና አገሩን በሚገባ ማገልገል ይችላል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው እንደ ሚዲያ ተቋም መጽሃፍትን አሰባስቦ ማስረከብ አገርን ለማዳንና ትውልድ ለመገንባት ያለውን ፋይዳ ገልጸዋል።

መጽሃፍቶቹ በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመፍታት፣ ማንነትን በማወቅ፣ አንድነትን በማጠናከር የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ አስረድተዋል።

በመሆኑም መሰል በጎ ተግባራትን መፈጸም የዜግነት ግዴታ አካል በመሆኑ ሁሉም እውቀትን እንዲያጋራ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)ን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ለአብርሆት ቤተ መፅሓፍት የሚያደርጉትን መጽሓፍ የማሰባሰብ መርሃ ግብር ቀጥለዋል።

የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍትን በመጻሕፍት ለመሙላት ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 29/2014 ዓ.ም የሚቆይ የመጻህፍት ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር እንደሚካሄድ ዛሬ ይፋ ተደርግል።

አብርሆት ቤተ-መጻህፍቱ አራት ሚሊዮን መጻህፍት የመያዝ አቅም አለው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም