ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር የተገበራቸውን የሌላቸውን የመደገፍና የመተጋገዝ ተግባር የዘወትር ሊያደርገው ይገባል-ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር የተገበራቸውን የሌላቸውን የመደገፍና የመተጋገዝ ተግባር የዘወትር ሊያደርገው ይገባል-ምክር ቤቱ
ባህርዳር ሚያዝያ 21/2014 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር የተገበራቸውን የሌላቸውን የመደገፍና የመተጋገዝ ተግባር የዘወትር ሊያደርገው እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ የኢድ አል ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸህ ሰይድ ሙሃመድ በመግለጫቸው ባስተላለፉት መልእክት በዓመት አንድ ጊዜ የሚገኘው የረመዳን ፆም ከመቸውም ጊዜ በላይ መተዛዘንና መደጋገፍ ጎልተው የሚታዩበት ወቅት ነው።
ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር የተገበራቸውን የሌላቸውን የመደገፍና የመተጋገዝ ተግባር የዘወትር ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
"በዓሉን ሲያከብርም ዘካ በማውጣትና የተቸገሩትን በመርዳት መሆን ይጠበቅበታል" ብለዋል።
ሰሞኑን በጎንደር ከተማ የተፈጠረው ችግር አሳፋሪና የኢትዮጵያዊያንን የዘመናት አብሮ የመኖር እሴት የሚያቆሽሽ መሆኑን አመልክተዋል።
መንግስት ችግሩ እንዲፈጠር ያደረጉትን ግለሰቦችን ለይቶ ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።
ጎንደር ለይ የተፈጠረው ግጭት እንዲባባስ ከሚገፋፉ አካላት መጠንቀቅ እንደሚገባ ጠቁመው "ህዝቡ የጠላት መጠቀሚያ እንዳይሆን ነገሮችን በሰከነ መንገድ መመዘን አለበት" ብለዋል።
"መሰል ግጭቶች ተያይዞ መጥፋት ካልሆነ በስተቀር አሸናፊ አይኖራቸውም" ያሉት ሸህ ሰይድ ችግር ፈጣሪዎች ተለይተው ለህግ ሊቀርቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።