የምሥራቅ አፍሪካ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት በቀጠናው ሰላምና ደኅንነት ለማረገጋጥ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የምሥራቅ አፍሪካ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት በቀጠናው ሰላምና ደኅንነት ለማረገጋጥ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል
ሚያዚያ 21 / 2014 (ኢዜአ) የምሥራቅ አፍሪካ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት በቀጠናው ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥሩ የተጠባባቂ ኃይሉ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ጌታቸው ሽፈራው ገለጹ።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን የአገር ሽማግሌዎች ሥልጠና ዛሬ አጠናቋል።
የአገር ሽማግሌዎቹ ሥልጠና የተጠባባቂ ኃይሉን አጠቃላይ ግዳጅ አፈጻጸምና ሥራቸውን ለመሥራት የሚያስችላቸው መመሪያ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር ተብሏል።
የተጠባባቂ ኃይሉ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ጌታቸው ሽፈራው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በሥልጠናው ተጠባባቂ ኃይሉ ያለበት የዝግጁነት ደረጃ ማሳወቅ መቻሉን ገልጸዋል።
በሥልጠናው የተሳተፉ የአገር ሽማግሌዎችም በቀጠናው ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ሥራቸውን ለመሥራት የሚያስችላቸው በቂ እውቀትና ክህሎት መጨበጣቸውን ጠቁመዋል።
ተጠባባቂ ኃይሉ ማንኛውንም ግዳጅ ለመፈጸም በበቂ ቁመና ላይ እንደሚገኝም በመጠቆም።
በቅርቡ የተቋቋው የአገር ሽማግሌዎች መማከርትም ለተጠባባቂ ኃይሉ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
ችግሮች በወቅቱ እንዲፈቱ በማድረግ እንዲሁም ግጭቶች ከመፈጠራቸው የመከላከል ሥራ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ነው ያነሱት።
የአገር ሽማግሌዎቹ አስቀድመው የግጭት ምልክቶችን ለአባል አገራት በማሳወቅ ከግጭት ነጻ አካባቢን ለመፍጠር እንደሚያግዙም ጠቁመዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የአገር ሽማግሌዎች መድረክ አባል አምባሳደር መሀሙድ ድሪር በበኩላቸው የአገር ሽማግሌዎች በሰላም ግንባታ ላይ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ወጣቶች የሰላም ባህል እንዲኖራቸውና ግብረገብነትን እንዲያዳብሩም አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል። ለዚህም የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ በመጠቆም።
የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ላይ ነበር የቀጣናው አገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ያጸደቁት።