የኢትዮጵያ ልዩ መገለጫ የሆኑ የህዝብ አብሮነትን የሚያጠናክሩ ዕሴቶች ሊጠበቁ እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልዩ መገለጫ የሆኑ የህዝብ አብሮነትን የሚያጠናክሩ ዕሴቶች ሊጠበቁ እንደሚገባ ተመለከተ
ሀዋሳ ሚያዝያ 21/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልዩ መገለጫ የሆኑና እንደ ፊቼ ጨምባላላ ያሉ የህዝብ አብሮነትን የሚያጠናክሩ ዕሴቶች ሊጠበቁ እንደሚገባ ተመለከተ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳና የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ዛሬ በሀዋሳ በተከበረው የፊቼ ጨምባላላ በዓል ላይ መልዕክት አስተላለፈዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ለሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው "በዓሉ የዓለም ህዝብ በዓል በመሆኑ እንዳይጠፋ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል" ብለዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የደስታና የይቅርታ በዓል እንደሆነ አመልክተዋል ።
"አሁን ላይ በተለያዩ መንገዶች ሕዝብን ለመከፋፈል የሚደረግ እንቅስቃሴን ባህላዊ ዕሴቶችን ተጠቅመን ማስቆም ይገባል" ያሉት ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያን ወደ አንድነትና አሸናፊነት ክብሯ መመለስ ይገባናል" ሲሉ አሳስበዋል ።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው የሲዳማ ህዝብ ከሌሎች ከኢትዮጵያ ወንድም ህዝቦች የሚጋራው እሴት እንዳሉት ሁሉ፤ የራሱ እሴቶች ባለቤት መሆኑን አስታውቀዋል።
''ፊቼ ጫምባላላ የአብሮነታችን ገመድና ሰዎችን ከሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ከእንስሳት ጋር በማስተሳሰር ሰላም ማውረድ የሚያስችል እሴቶች ባለቤት ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።
ፊቼ ጨምባላላ ባለው ትውፊት በዓለም ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ በዩኔስኮ የተመዘገበ ሀብት መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።
ሀብቱን አልምቶና አስተዋውቆ የሀብቱ ባለቤት የሆነውን ህዝብ እንዲጠቅም ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በሀዋሳ ከተማ ጉዱማሌ አደባባይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች የተሳተፉበት የዘንድሮው የፊቼ ጨምባላላ ክብረ በዓል ዛሬ ተጠናቋል።