በወራቤ ከተማ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ውሎ መረጋጋቱን ፖሊስ አሰታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በወራቤ ከተማ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ውሎ መረጋጋቱን ፖሊስ አሰታወቀ
ሀዋሳ ሚያዚያ 21/2014(ኢዜአ)....በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ አስተዳደር ትናንት ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር አሁን ላይ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ መረጋጋት መምጣቱን የከተማው አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ኑረዲን አምደላ ለኢዜአ በስልክ እንደገለጹት ትናንት ከቀኑ 7:00 ሰዓት ጀምሮ የጥፋት ተልዕኮ ባነገቡ ጥቂት ግለሰቦች በአካባቢው የፀጥታ ችግር ተከስቷል።
በጎንደር ሰሞኑን ተከስቶ የነበረውን አስነዋሪ ድርጊት ማውገዝ በሚል ሰበብ በጥቂት ግለሰቦች የተጀመረው ሂደት ከታሰበው ውጭ ወደ አለመግባባት ማምራቱን ተናግረዋል።
በዚህም በኃይማኖት ተቋማት ንብረትና በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ዋና ኢንስፔክተር ኑረዲን ተናግረዋል።
የፀጥታ ኃይሎች ክስተቱን ለመቆጣጠር የቀናጀ ጥረት በማድረጋቸው በቁጥጥር ስር ውሎ አካባቢው መረጋጋቱን ተናግረዋል።
የኃይማኖት አባቶችንና ወጣቶችን በማሳተፍ የተሰራው የፀጥታ ስራ ለመረጋጋቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል።
የከተማዋ ሰላምና መረጋጋት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከኃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ከእምነቶቹ ተከታዮች ጋር በቅርበት ምክክር በማድረግ አካባቢው የሚታወቅበት ሰላምና አብሮነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል ስራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ለፀጥታ ችግሩ መነሻ ምክንያትና እጃቸው ያለበትን ግለሰቦች አጣርቶ ለህግ የሚያቀርብ አጣሪ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደስራ መግባቱን ተናግረዋል።
ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሀገርን የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ በግልፅም ሆነ በስውር የሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለህግ ለማቅረብና ለማረም የፀጥታ ኃይሉ ከኅብረተሰቡጋር በትጋት እንደሚሰራም ዋና ኢንስፔክተር ኑረዲን አረጋግጠዋል።