ከሃይማኖት አስተምህሮ ውጭ የሚስተዋል ድርጊትን እናወግዛለን- የደሴ ከተማ ሀይማኖት አባቶችና ህዝባዊ ተቋማት - ኢዜአ አማርኛ
ከሃይማኖት አስተምህሮ ውጭ የሚስተዋል ድርጊትን እናወግዛለን- የደሴ ከተማ ሀይማኖት አባቶችና ህዝባዊ ተቋማት
ደሴ ሚያዚያ 21 2014 (ኢዜአ) ከማንኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ ውጭ የተደረገው አስነዋሪ ተግባር ሀገርና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በጋራ ሆነን እንታገላለን ሲሉ የደሴ ከተማ የሐይማኖት አባቶችና ህዝባዊ ተቋማት ህብረት አስታወቁ።
የደሴ ከተማ ሐይማኖት አባቶችና ህዝባዊ ተቋም በጎንደር የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተወካይ መላከ ብርሃናት ገብረጻዲቅ አስፋው እንደገለጹት በጎንደር ከተማ የተፈፀመው ጥቃት የማንም ሀይማኖት የማይወክል አስነዋሪና ፀያፍ ተግባር ነው፡፡
የየትኛውም ሀይማኖት አገር እንዲፈርስ የሚፈቅድ አስተምሮ እንደሌለው ጠቁመው፤ ወንድምን መግደል፣ ቤተ እምነትን ማቃጠል ቀርቶ ክፉ ማሰብ እንኳ በየሀይማኖቱ የተጠላና የተወገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ሁሉም ከዚህ አስነዋሪ ተግባር መጠንቀቅ እንደሚገባው ጠቅሰው፤ "ተንኮለኞች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ መሆኑን በመገንዘብ አገር በሴረኞች እንዳትፈርስ በጋራ ልንቆም ይገባል" ብለዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ህዝባዊ መጅሊስ ፕሬዚዳንት ሸህ እንድሪስ በሽር በበኩላቸው "በጎንደር ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ከሁላችንም ሀይማኖት የወጣ አሳፋሪ ተግባር ነው" "የደረሰውን ጉዳት አጥብቀን እናወግዛለን፣ በየትኛውም ሀይማኖት ላይ ጥቃት እንዲፈጸምም አንፈቅድም፣ በጋራ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ እንሰራለን" ብለዋል።
"መንግስት አጥፊዎችን ነጥሎ ለህግ በማቅረብ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ለህዝብ ይፋ ማድረግ አለበት" ያሉት ሸህ እንድሪስ "በተለያዩ አካባቢዎች ተጨማሪ ጥፋት እንዳይመጣ ህዝቡ መጠንቀቅና ከመንግስት ጋር መስራት ይገባዋል" ሲሉ አስገንዝበዋል።
''በጎንደር የደረሰው ጉዳት የማንንም ሀይማኖት የማይወክል፣ አጥብቀን የምናውግዘው ድርጊት ነው'' ያሉት ደግሞ የደሴ መካነየሱስ ቤተ ክርስቲያን መሪ ቄስ መስፍን ጌታሁን ናቸው፡፡
ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም በየሀይማኖቱ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
የደሴ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቆሞስ አባ ማቲያስ ፍሊጶስ በበኩላቸው "እምነትን ሽፋን አድርገው በመካከላችን የተደበቁ ሴረኞችን አጋልጠን በመስጠት አንድነታችንን አጠናክረን ኢትዮጵያን ማዳን አለብን" ብለዋል።
"ተንኮል እንዲቆም ሁላችንም መጸለይና መስራት እንዲሁም የሰላም መሳሪያና ተምሳሌት ልንሆን ይገባል" ሲሉም አመልክተዋል።
''ህብረተሰቡ አንድነቱን አጠንክሮ አካባቢውን በንቃት ሊጠብቅ ይገባል እንጅ በአሳፋሪ ተግባር መሳተፍ የለበትም'' ያሉት ደግሞ የደሴ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን አስተባባሪ ወንጌላዊ መላኩ ብርሃኑ ናቸው፡፡
የደሴ ከተማ ሴት ነጋዴዎች ተወካይ ወይዘሮ ዕፀገነት ታደስ በበኩላቸው "በጎንደር የደረሰው ጉዳት ሁላችንንም አሳፍሮናል፤ አሳዝኖናልም" ብለዋል፡፡
"እንዲህ አይነት የታሪክ ጠባሳ እንዳይደገም በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በተለይ ሴቶች ቤተሰቦቻችንን በመመክር ኢትዮጰያን መታደግ ይገባናል" ሲሉ አመልክተዋል።
የደሴ ከተማ የሀይማኖትና ህዝባዊ ተቋማት በጎንደር የተፈጸመውን ድርጊት የሚያወግዝ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡