የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ ዕርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ ዕርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ
ሚያዚያ 21/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ ዕርዳታ ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳምንቱ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብትና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ዋና ዋና ሁነቶችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ረገድ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አብራርተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ያለምንም መስተጓጐል የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ምንም አይነት የዕርዳታ ድርጅት አለመገደቡን ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል።
''የሁለት ሶስት ቀናትን ሳይጨምር 146 የሚሆን 'ኮንቮይ' ወደ ትግራይ ደርሰዋል" ነው ያሉት አምባሳደር ዲና ከነዚህ ውስጥ ዘጠኙ የነዳጅ ጭነት መሆኑን አብራርተዋል።
የለጋሽ ድርጅቶች እጥረትና የተረጂዎች ቁጥር መጨመር እንዳለም ጨምረው ገልጸዋል አምባሳደሩ።
አሸባሪው የሕወሓት በአፋር ክልል ከያዛቸው ቦታዎች እንዲወጣ ቢጠየቅም አንዳንድ ቦታዎችን አለመልቀቁን ገልጸዋል።
በመሆኑም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የዕርዳታ እጁን እንዲዘረጋና የሕወሓት ታጣቂዎች በአፋር ክልል ከያዟቸው ቦታዎች ለቀው እንዲወጡ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን በማስመለስ ሂደት እስካሁን ከ15 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በሳምንቱ በምጣኔ ሀብት ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ተግባራትንም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አብራርተዋል።