አዲሱ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ለትውልዱ ብሩህ ተስፋ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ለትውልዱ ብሩህ ተስፋ ሆኗል
አስመራ ጶጉሜን 2/2010 በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ሰላምና እየተጀመረ ያለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ብሩህ ተስፋ እንደሆናቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የአስመራ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። እርቀ ሰላሙን ከማውረድ ባለፈ የዜጎችን ጥቅም የሚያረጋግጡ ስራዎች በተግባር መታየት መጀመራቸውም ለነገ ተስፋ እንደሆናቸው ነው ነዋሪዎቹ የገለፁት። ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ20 ዓመታት የጠላትነት ፍረጃ ወጥተው ወደ ሰላም ከተመለሱ ከሁለት ወራት ጊዜ ያልዘለለ እድሜ ቢያስቆጥርም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ግንኙነቱን ወደ ጤናማ ግንኙነት የመመለስ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። ከነዚህም መካከል የመሪዎች ምክክርና የተፈረሙ ስምምነቶች፣ የኤምባሲዎች መልሰው መከፈት፣ የአየርም ሆነ የየብስ ትራንስፖርት መጀመር፣ አሁን ደግሞ የጋራ የወደቦች አጠቃቀም ማስጀመር ይጠቀሳሉ። ወጣቶችም የተረጋጋ ቀጠና ውስጥ መኖርና የስራ እድል ማግኘትን ተስፋ አድርገዋል። ዮናታን ዮሃንስ የተባለው ወጣት ሁለቱ አገር እያደረጉት ያለውን ግንኙነት በተመለከተ እንደተናገረው የዜጎችን ጥቅም የሚያረጋግጡ ስራዎች በተግባር መታየታቸው ለወጣቱም የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ አስደስቶኛል ብሏል። ‘’ ሁለት አገራት የቆየ ግጭት ነበራቸው፣ አሁን ግን ሁሉ ነገር ሰላም ሆነዋል፣ እኔም በጣም ደስ ብሎኛል ኩራት ተሰምቶኛል፣ ምክንያቱም የሁለቱ አገራት ህዝቦች በባህል ብዙ ነገር የተሳሰሩ ናቸው። ስለዚህ አሁን እኛም የተሻለ ተስፋ እንዲንሰንቅ ያደርገናል።’’ ሲል የተናገረው ደግሞ ወጣት ሳሚ ሙሃመድ ኑር ነው። ወጣት መሀመድ ተፈሪ በበኩሉ ወደቡ መከፈቱም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በጣም የሚያቀላጥፍ መሆኑን ተናግሯል። ኢዜአ ያነጋገራቸው እናቶች ደግሞ እነርሱ ያዩትና ያሳለፉት አስከፊ ታሪክ እንዳይደገም፣ የተሻለ ነገር ለልጆች ማውረስን ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ወይዜሮ ጸጋ ሰለሞን እንደሚሉት አሁን በሁለቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ያለው ግንኙነት ለኢትዮጵያና ኤርትራ በጣም ደስ የሚያሰኝ ልጆቻቸውም እነሱ የኖሩትን እንዳይደግሙና የተረጋጋ ነሮ እንድሮሩ የሚረዳ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ መርከብ በምጽዋ ወደብ ስራ መጀመሯና ትናንት ደግሞ የኢትዮጵያ ኢምባሲ በአስመራ ከተማ መከፈቱ ይታወሳል።