በባሌ ዞን የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲባባሱ ባደረጉ 460 የመንግስት ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲባባሱ ባደረጉ 460 የመንግስት ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ
ጎባ ሚያዚያ 21/2014/ኢዜአ/ በባሌ ዞን ከመስሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲባባሱ ባደረጉ 460 የመንግስት ሰራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ።
የዞኑ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ዋዶ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ተገልጋዩ ማህበረሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የመንግስት የስራ ሰዓትን አለማክበር፣ በእቅድ አለመመራት፣ የተቀመጡ ደረጃዎችን አክብሮ አለመስራትና ባለጉዳይን ማጉላላት ከተለዩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
"በዞኑ አስራ አንድ ወረዳዎች ውስጥ ለዚሁ ተብሎ የተቋቋመ ግብረ ኃይል ከህብረተሰቡ የቀረበለትን ቅሬታና በተለያዩ ጊዜያት ባደረገው ድንገተኛና መደበኛ ክትትልና ግምገማ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተቶች መስተዋላቸውን አረጋግጧል" ብለዋል ፡፡
ግብረ ኃይሉ በመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት ከችግሩ ጋር በተደጋጋሚ የሚነሱ ሰራተኞችን ክፍተት ለመሙላት አጫጭር ስልጠናዎችን መስጠቱንም አመልክተዋል፡፡
አቶ ከድር እንዳሉት የተሰጣቸውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመጠቀም ራሳቸውን ማሻሻልና መለወጥ ባልቻሉና የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት የፈጠሩ 460 የመንግስት ስራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡
ከሰራተኞቹ መካከል 24ቱ ከስራ እንዲሰናበቱና 15ቱ ከደረጃ ዝቅ እንዲሉ ሲደረግ 14ቱ የፈጸሙት ጥፋት የሚያስከስስ በመሆኑ ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም 67ቱ በደሞዝ፣ 104ቱ በጽሁፍና 207ቱ በቃል ማስጠንቀቂያ እንዲቀጡ ተደርጎ ቀሪዎቹ ከነበሩበት ቦታ ወደሌላ ክፍል ተዛውረው እንዲሰሩ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ኃይሌ "በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተቀምጠው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚያባብሱ ሰራተኞች ከህብረተሰቡ የሚቀርቡ መረጃዎችን በማጣራት አስፈላጊው እርምጃ መውሰዱ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡
ህዝቡም ይህን እውነታ በመገንዘብ ለመልካም አስተዳደር ተግባራዊነት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ከሮቤ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሼህ ሀሰን በከር በሰጡት አስተያየት መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በመለየት እልባት ለመስጠት እያደረገ የሚገኘው ጥረት የሚደነቅና ሊቀጥል የሚገባ ነው ብለዋል።
እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ በመንግስት ተቋማት ህዝቡን የሚያማርሩ ሰራተኞችን በማስተካከል ህዝቡ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ሲለሚያግዝ ለተግባራዊነቱ ጥቆማ በመስጠት እንደሚተባበሩ የገለጹት ደግሞ አቶ አህመድ መሐመድ ናቸው፡፡