ቀጥታ፡

ሠራተኛው ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ተጠየቀ

ሚያዚያ 20/2014/ኢዜአ/ ሠራተኛው ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን አሳሰበ።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀንን በማስመልከት ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ሠላም የህልውና መሰረት ነው ብለዋል።

በመሆኑም በተለያዩ ተቋማት የሚሰራው ሠራተኛው ማኅበረሰብም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት እንዲረጋገጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ምርታማነት ከሌለ ሠራተኛ፣ አሰሪና መንግሥት መኖር አይችልም፤ በመሆኑም አሰሪና ሠራተኛ ለምርታማነት ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።  

መንግሥት የሠራተኛውን የመደራጀት መብት በመከልከል የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ የሠራተኞችን የመደራጀት መብት እንዲያከብርና እንዲያስከብርም ጠቁመዋል።

ሠራተኞች አሁን ላይ በሚከፈላቸው ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ባለመቻሉ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።  

ዝቅተኛ የደመወዝ ቦርድ ወለል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቢቋቋምም ወደ ሥራ እንዲገባ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በሥራ ቦታ የሙያ ደኅንነት ጤንነት መከላከልን አስመልክቶ የወጡ ሕጎች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።  

የዘንድሮውን ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይከበራል ተብሏል።

ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ133ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ47ኛ ጊዜ "የሰራተኛው መደራጀት ለሰላም፣ ለምርታማነትና ለኑሮ መሻሻል"በሚል ሐሳብ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም