ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴታቸውን የሚሸረሽሩ ድርጊቶችን በስክነት ማየት ይኖርባቸዋል-የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አባል

ሚያዚያ 21/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያውያን የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴታቸውን የሚሸረሽሩ ድርጊቶችን በሰከነ መንገድ ማየት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አመራር አባል መከሩ።

የኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አመራር አባል ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ በጎንደር ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በተከሰተው ግጭት ዙሪያ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ድርጊቱ ተደጋግፈውና ተቻችለው እየኖሩ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የማይወክል መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን ተከባብረው በአንድነት የመኖር ማህበራዊ እሴታቸውን ለመሸርሸር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በጋራ መመከት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ሃይማኖትና ብሔርን ሽፋን በማድረግ ግጭት የሚቀሰቅሱ ሃይሎች መጠቀሚያ ባለመሆን ነገሮችን ቆም ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በእንደዚህ አይነት ግጭቶች ህይወታቸው የሚያልፈውና የሚጎዱት ንጹሃን ዜጎች እንጂ ከኋላ ሆነው አጀንዳ የሚሰጡ አካላት አለመሆናቸውንም ገልጸዋል።

ይህንን በመገንዘብ ግጭቶች እንዳይባባሱና ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመቱ በሰከነ መንፈስ መነጋገርና ቀደም ሲል የነበረውን የመቻቻል፣ የመስማማት፣ አብሮ የመኖር እሴቶችን ማጎልበት  ተገቢ መሆኑን አክለዋል።

ኢትዮጵያ ላላት የዳበረ የአገር ሽምግልና እና ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ትኩረት በመስጠት ችግሮች ሳይሰፉ መፍታት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ብሔርና ሃማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭት መፍጠር አገርን ወደ ኋላ የጎተተ አካሄድ በመሆኑ ውይይት የሚያስፈልግበት ወሳኝ ጊዜ መሆኑንም በአጽእኖት አንስተዋል።

"ኢትዮጵያዊ ያደረጉን ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው፣ የሚያስማሙን የትኞቹ ናቸው፣ የሚያለያዩን የትኞቹ ናቸው ብለን ቁጭ ብለን እንወያይ" ሲሉ መክረዋል።

በሃይማኖትና በብሔር በመሸሸግ ህዝብና አገርን ከመጉዳት ኋላቀር አካሄድ በመውጣት ሁሉም በጋራ የሚኖርባትን አገር መፍጠር አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።

ከህግ በላይ የሚሆን አካል ባለመኖሩ መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ በማቅረብ አስተማሪ ርምጃ መውሰድ እንዳለበትም የኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አመራር አባል ዶክተር ሙሉጌታ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም