ቀጥታ፡

የፊቼ ጨምባላላ በዓል በጉዱማሌ አደባባይ እየተከበረ ነው

ሀዋሳ ሚያዝያ 21፣ 2014 (ኢዜአ) የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምባላላ በዓል በሀዋሳ ከተማ ጉዱማሌ አደባባይ እየተከበረ ነው።

በዓሉ  በክልሉ በሁሉም መዋቅሮችና በተለያዩ ተቋማት ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የመጡ የብሄሩ ተወላጆችና የበዓሉ ታዳሚዎች የተሳተፉበት የፍቼ ጫምባላላ በዓል ዛሬም ደማቅ በሆነ የሲዳማ ባህላዊ ሥነ-ሥርዓት በሀዋሳ ከተማ በጉዱማሌ አደባባይ በድምቀት እየተከበረ ነው።

እየተከበረ ያለው ዛሬ ከንጋት ጀምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ የባህሉ ባለቤቶች በባህላዊ አልባሳት ደምቀው በቄጣላና ሌሎች ልዩ ልዩ  ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ነው።

በበዓሉ ላይም የኢፌዴሪ  የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር  ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላና የኢፌዴሪ አየር ሀይል አዛዥ ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እንዲሁም የተለያዩ ሚኒስትሮች ፣አምባሳደሮችና ሌሎች የፌዴራልና ክልል  የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የፊቼ ጨምባላላ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ደርጅት(ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ ስድስት  ዓመታት ማስቆጠሩ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም