በጎንደር ከተማ ግጭት በፈጠሩ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል- ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ

472

ባህር ዳር ሚያዚያ 20/2014 ዓ/ም... በጎንደር ከተማ ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭት የፈጠሩ አካላት ላይ ተገቢውን ማጣራትና ክትትል በማድረግ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ሰሞኑን ጎንደር ከተማ ጥቃቅን ግጭት መንስኤ በማድረግና አድማሱን በማስፋት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

የክልሉ መንግሥት የመልሶ ግንባታውን ባለጠናቀቀበት እንዲህ አይነት ግጭት ተፈጥሮ የሰው ሞትና የንብረት ውድመት በመከሰቱ ጥልቅ ሃዘን የተሰማው መሆኑን ገልጸው፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

ይህ አስነዋሪ ድርጊት አጠቃላይ ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ወደ ባሰ ምስቅልቅል ለማስገባትና ኢትዮጲያን ለማተራመስ የታሰበ እንጂ ማንንም የማይጠቅም ድርጊት መሆኑን በአፅኖት ገልፀዋል።

"ጉዳዩን ማንም ያስነሳው ማንም ያድርገው እኔ በጽኑ የማወግዘውና መላ ህዝባችንም እያወገዘው የሚገኝ እኩይ ድርጊት መሆኑን ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግሥት የተፈጠረውን ችግር በማስቆም በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ክትትልና ማጣራት በማድረግ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ዶክተር ይልቃል አረጋግጠዋል።

ይሁን እንጂ የተፈጠረውን ችግር በማስፋፋትና ወደ ትርምስ ለማስገባት ኢትዮጵያን አደጋ ውስጥ መጣል ለማንም ኢትዮጵያዊ የማይጠቅም መሆኑን መላ ህዝባችን እንዲገነዘብ እፈልጋለሁ ብለዋል።

መንግሥትና የኃይማኖት አባቶች እያደረጉት ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት በመደገፍና ከጎናቸው በመቆም የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በመነጋገር መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሁሉም የክልላችን ህዝብና መላው ኢትዮጵያውያን ይህን መሰል ችግር የምንፈታውና ኢትዮጵያን በጋራ በማጽናት ለሁሉም አማኞች እኩል የምታገለግል ሀገር የምናደርገው ሰላምን በአስተማማኝ ደረጃ ስናረጋግጥ ብቻ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ።

ይህን ሁሉም አካል በመገንዘብ የተጀመረው የሰላም ፍሬ እንዲያፈራ በያለበት ሆኖ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም