አጥፊውን አውግዘን ከተጠቂው ጋር እንቆማለን እንጂ ጥፋቱን በሌላ ጥፋት ለማባባስ መሞከር የለብንም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
አጥፊውን አውግዘን ከተጠቂው ጋር እንቆማለን እንጂ ጥፋቱን በሌላ ጥፋት ለማባባስ መሞከር የለብንም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
ሚያዚያ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) አጥፊውን አውግዘን ከተጠቂው ጋር እንቆማለን እንጂ ጥፋቱን በሌላ ጥፋት ለማባባስ መሞከር የለብንም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስገነዘቡ።
እንደ ህዝብ ልዩነቶቻችንን አምነን ተቀብለን በብዙ ትውልዶች ዕድሜ በኁባሬ ተሣሥረን ኖረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በጋራ ስፌታችን ውስጥ መቻቻል አንዱ አስፈላጊ ሰበዝ ነው ብለዋል።
እንደ አንድ ሕዝብ፣ የሀገራችንን መጥፋት የሚፈልጉ ሁሉ፣ የጥፋት ዕቅዳቸው ወኪል አድርገው እንዲወስዱን ልንፈቅድ አይገባም በማለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ እንዲሆን የምንፈቅድለት ክፋት ከእርስ በርስ ተዛምዷችን ጋር ካለው ቅርበት ይልቅ ለሌሎች የጥፋት ወኪሎች መጠቀሚያ የሚሆን ነው ብለዋል።
በማኅበረሰባችን ውስጥ የአስተዋዮችን ልቡና እንፈልግ እና ልዩነቶችን ከማጉላት ይልቅ ለማቀራረብ እንሥራ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የምንጋራው ሰብአዊነት ይህንን እንድናደርግ ያስገድደናል ሲሉ ገልጸዋል።
ማንንም ለማጥፋት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ጥቃት በሁላችን ላይ የሚደረግ ነው ብለዋል።
አጥፊውን አውግዘን ከተጠቂው ጋር እንቆማለን እንጂ ጥፋቱን በሌላ ጥፋት ለማባባስ መሞከር የለብንም ሲሉም አስገንዝበዋል።
ከኢትዮጵያ ሰላም እንጂ ከኢትዮጵያ ሑከት ማናችንም አናተርፍም በማለትም ገልጸዋል።