ቀጥታ፡

ኢንጅነር ስመኘው ራሳቸውን ማጥፋታቸውን አረጋግጫለሁ- ፌዴራል ፖሊስ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2010 የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ራሳቸውን ማጥፋታቸውን በምርመራ እንዳረጋገጠ የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ። ከህዳሴ ግድብ መጓተት ጋር ተያይዞ አገሪቱ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጓና ለብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ካለአግባብ የተፈጸመው ክፍያ በፈጠረባቸው መጨናነቅ እራሳቸውን እንዲያጠፉ መንስዔ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገልጿል። የፌዴራል ፖሊስ ይህን ያለው ዛሬ የኢንጅነር ስመኘው አሟሟትን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ እንዳሉት፤ ኢንጂነሩ ሞተው በተገኙበት መስቀል አደባባይ ፖሊስ በዕለቱ 2 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ ደርሷል። በቦታው የደረሰው ፖሊስ ምናልባት ኢንጅነሩ በህይወት ካሉ ለማትረፍ በሚል ምክንያት የተቆለፈው መኪናቸውን ሰብሮ መግባቱን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ኢንጅነሩን ግን በህይወት ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸዋል። ፖሊስ ሟች ሲገለገሉባቸው የነበሩ የተለያዩ ንብረቶችን መኪናው ውስጥ ማግኘቱንም ጠቁመዋል። "ከዚያው ተሽከርካሪ ውስጥ አንድ ኮልት ሽጉጥ አግኝተናል። ቀለሃና እርሳስ እንዲሁም ያልተተኮሱ ጥይቶች አግኝተናል። ሟች ይጠቀሙበት የነበሩ ሁለት ስልኮችን፤ ሁለት ካኪ ፖስታዎችን ከመኪናው ውስጥ አግኝተናል። በወቅቱም ሟች ይጠቀሙት የነበረው ተሽከርካሪ በሮች የተዘጉ መሆናቸውን አረጋግጠናል። በወቅቱ የወንጀል መከላከል አመራር በመኪናው ውስጥ ያሉት ኢንጂነሩ መሆናቸውን ሲያይ በህይወት ጣር ላይ ከሆኑ ለማዳን በሚል ሟችን በህይወት ለማዳን ሲሉ በሩን ሰብረው ገብተው በኋላ ሲረጋገጥ ህይወታቸው ማለፉን አረጋግጠናል።” የሽብር ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር አለማየሁ ሃይሉ ኢንጂነር ስመኘው አደጋው በደረሰ ዕለት በጠዋት ከቤታቸው መውጣታቸውንና ሞተው በተገኙበት አካባቢ ሁለት ጊዜ መታየታቸውን ተናግረዋል። ፖሊስ ኢንጂነሩ ቢሯቸው ከገቡ በኋላም በተደጋጋሚ ወደ መጸዳጃ ቤት ሲመላለሱ እንደነበር ከአይን እማኞች ማረጋጋጡንም አክለዋል። "ጠዋት 12፡45 ሲሆን ነው ከመኖሪያ ቤታቸው የወጡት ከዛም ከ15 ደቂቃ ጉዞ በኋላ መስቀል አደባባይ እዛው መኪናው ቆማ በተገኘችበት ቦታ የነበሩ መሆኑን፤ ከ5 ደቂቃ በኋላ ወደ ቢሯቸው ተመልሰው የገቡ መሆኑን የምርመራ ቲሙ ያረጋገጠ ሲሆን ከአካባቢው የተገኙ ማስረጃዎች በወቅቱ እዛው ቦታ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የተገኙ መሆናቸውን ጭምር ማረጋገጥ ተችሏል። ልክ 1፡05 ላይ ቢሯቸው ገብተው በወቅቱ የነበሩ የጥበቃ ሰራተኞች የጽዳት ሰራተኞች ያዩቸው ስለነበር የእሳቸውን እንቅስቃሴ እስከ 1፡45 እዛው ቢሯቸው ቆይተው 1፡45 ጀምሮ ወደ መጸዳጃ ቤት ይመላለሱ እንደነበር ከተገኘው መረጃና ማስረጃ ማረጋገጥ ችለናል።” ከ2 ሰዓት ጀምሮም ሾፌራቸውን ጨምሮ ለሌሎች የስራ ባለደረቦቻቻው እየደወሉ የተለያዩ ፖስታዎችን እንደሰጡም የምርመራ ቡድኑ ማረጋገጡን ኮማንደር ዓለማየሁ ገልጸዋል። "ልክ 2ሰዓት ላይ እዛው ቢሯቸው ሆነው ሁለት ሾፌሮች አሏቸው አንደኛውን ሾፌር ና የምትወስደው መልዕክት አለ ብለው 2 ሰዓት ላይ እንደደወሉ የታሸገ ፖስታ ሰጥተው ለማን እንደምትሰጥ እነግርሃለሁ ብለውት እንደሄዱ፤ እሱም የሰጭውን ስልክ በመጠባበቅ ላይ እያለ ሌላ አትክልተኛና የጽዳት ሰራተኛ ለእርሱም በተመሳሳይ በሞባይል ስልኩ ደውለው ካስመጡት በኋላ አንድ ፖስታ በተመሳሳይ የታሸገ ወደ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አካባቢ ታደርሳለህ ብለውት እንደነበርና ፖስታውን ተቀብሎ ልክ 2፡20 ወደ እርሳቸው ደውሎ ደርሻለሁ ቦታው ላይ ለማን ነው የምሰጠው ብሎ ሲጠይቃቸው ጠብቀኝ ብለውታል፤ 2፡21 ላይ ደግሞ ለጸሃፊያቸው ደውለው መምጣት ትቺያለሽ ብለው እንደጠየቋት፤ እሷም መምጣት እንደማትችል በኋላም መልሰው ሁለት ፖስታዎችን ቢሮ እንዳስቀመጡላት፤ አንዱ ፖስታ ለእርሷ ሌላኛውን ስጭ ለምልሽ ሰው ትሰጫለሽ በሚል እንደነገሯት፤ ልክ 2፡21 ላይ መኪናዋ ቆማበት ወደ ነበረው መስቀል አደባባይ እንደመጡ አረጋግጠናል።" ይህም ኢንጅነሩ ከሞቱበትና ፖሊስ በስፍራው በተገኘበት መካከል የዘጠኝ ደቂቃ ብቻ ልዩነት መኖሩን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል። የኢንጅነሩን አሟሟት በተመለከተ ማጠቃለያ የሰጡት የፌዴራል ፖሊስ ጄነራል ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ኢንጅነር ስመኘው በቀለ እራሳቸውን ማጥፋታቸውን በፖሊስ ምርመራ መረጋጋጡን ገልጸዋል። "አሟሟታቸውን በተመለከተ ኮንታክት ሹት በሚባለው አስደግፈው የተመታ መሆኑን አጠቃላይ በፎረንሲክና በሆስፒታል ምርመራ ድምዳሜ ላይ ደርሰናል። መኪናውን በተመለከተ ባለሙያዎች እንደገለጹት በምንም መልኩ ቪ8 ቶዮታ የሚባለው መኪና ሞተር እየሰራ በውጭ በኩል ማንም ሰው ዘግቶ ሊሄድ እንደማይችል ሞኤንኮ በጽሁፍ ጭምር በደብዳቤም ጭምር ገልጾልናልና አጠቃላይ ድምዳሜዎቹ ሲታዩ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በሰው በደረሰባቸው ጉዳት ህይወታቸው እንዳላለፈና አብዛኛው ኢንዲኬሽን ራሳቸውን እንዳጠፉ የሚያመላከት እንደሆነ ነው ምርመራው የሚጠቁመው።" ኢንጅነሩ ራሳቸውን ሊያጠፉ የቻሉበት ጉዳይ ጥልቅ ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ የገለጹት ጄነራል ኮሚሽነሩ፤ የህዳሴ ግድብ አፈጻጸም መዘግየትና ለሜቴክ ያለአግባብ የተፈጸሙ ክፍያዎች የፈጠሩባቸው መጨናነቅ እንደሆነ አመላካች መሆኑንም ጠቁመዋል። "ሰፊ ጊዜ የሚወስድ የተጀመሩ የምርመራ ጉዳዮች ያሉ ቢሆንም ፕሊምናሪ ኢንዲኬሽኑ ከስራቸው ቦታ ጋር ተያይዞ በተለይ የህዳሴ ግድቡ የስራ አፈጻጸም መዘግየት ጋር ተያይዞ ጋፕ በመፈጠሩ ጋፕ ብቻ አይደለም ብዙ ብዙ ተጨማሪ ወጭ ማስከተሉ ጋር ተያይዞ ከሜቴክ ጋር ተያይዞ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ጋር ያለው አፈጻጻም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ የተከፈለው ገንዘብ ደግሞ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ገንዘቡ ደግሞ ያለ እሳቸው አውቶራይዜሽን የማይከፈል መሆኑ ስለዚህ ስራው አለማለቁ የተከፈለው ገንዘብ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ሳሊኒ ደግሞ ስራው በመዘግየቱ ምክንያት 250 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ቫሪየሽን መጠየቁ እነዚህ ነገሮች ተዳምረው በኢንጅነሩ ላይ ከፍተኛ የሆነ መጨናነቅ የፈጠረ መሆኑ የምርመራው ውጤት ያመላክታል።" ለስራ ባልደረቦቻቸው የሰጧቸው ፖስታዎች ውስጥ ያሉት መልዕክቶች አብዛኛዎቹ ከስራቸው ጋር የተገናኙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለጸሃፊያቸው ከሰጧቸው ውስጥ ግን "የልጆቼን ነገር አደራ" የሚል ሃሳብ መኖሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም