እንደ አገር የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል ለማለፍ መተባበርና መከባበር ይገባል

178

ሚያዚያ 20/2014/ኢዜአ/ እንደ አገር የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል ለማለፍ መተባበር፣ መተጋገዝና መከባበር እንደሚገባ ከኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ጣምራ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ ተናገሩ፡፡

ኡስታዝ አቡበከር አህመድ 'ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት ጉዞ' ጥሪን ተቀብለው ለመጡ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡  

በንግግራቸውም ኢትዮጵያ ለእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከነበራቸው ቀደምት አገሮች  መካከል አንዷ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የነብዩ መሐመድ ተከታዮች በእምነታቸው ምክንያት ግፍ ሲደርስባቸው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሃይማኖታቸውን በነጻነት ማራመድ እንደቻሉም ነው የተናገሩት፡፡

ከሌሎች አካባቢዎች የተሰደዱ የእምነቱ ተከታዮችን የተቀበሉት የወቅቱ ንጉስም በነብዩ መሐመድ የተመሰከረላቸው እንደነበሩም አብራርተዋል፡፡

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ የአብሮነት እሴት ባፈነገጠ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች እጅግ አሳዛኝ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም እንደ አገር እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች በድል ለማለፍም እርስበርስ መተባበር፣መከባበርና መተጋገዝ ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም