ኅብረተሰቡን ያሳተፉ የጸጥታ ሥራዎች ከባድ ወንጀሎችን በመከላከል አበረታች ውጤት ተገኝቶባቸዋል

ሚያዚያ 20/2014/ኢዜአ/በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ኅብረተሰቡን ያሳተፉ የጸጥታ ሥራዎች በየአካባቢው የሚፈጸሙ ከባድ ወንጀሎችን በመከላከል አዎንታዊ ውጤት ማስገኘታቸውን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር አድማሱ ኢፋ እንደገለጹት፤ ክፍለ ከተማው ከነበረው ስፋትና ከሕዝቡ ብዛት አንጻር በርካታ ወንጀሎች የሚፈጸሙበት ነበር።

ባለፈው ዓመት ብቻ በአካባቢው በጦር መሳሪያ የታገዘ አስራ አራት ዘረፋዎችና በርካታ የተሽከርካሪ ስርቆቶች መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።

በሞተር ሳይክልና በመኪና ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መበራከታቸውንና  ውስብስብ ባህሪ እንደነበራቸው ገልጸዋል።

የከተማው አስተዳዳርና የከፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ በቅርቡ በጋራ በወሰዱት የአደረጃጃት ማሻሻያዎች ውጤቶች መገኘታቸውን አስረድተዋል።

በተለይም በክፍለ ከተማው በጦር መሳሪያ የታገዘ ከባድ ወንጀል ባለፉት ሦስት ወራት ሙሉ በመሉ በሚባል ደረጃ መቆሙን ነው ለአብነት ያነሱት።

የመኪና ስርቆትም ከግማሽ በላይ መቀነሱን ጠቅሰው የቅሚያ ወንጀሎች  በመከላከልም አብዛኞቹን ወንጀለኞች በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ኅብረተሰቡን በማሳተፍና ተቋማትን ጭምር እርስ በእርስ በማስተሳሰር የተሰራው የወንጀል መከላከል ሥራ ውጤት ማስገኘቱን ነው ያብረሩት።    

የፖሊስ የደንብ ልብስ በመልበስና ሃሰተኛ መረጃዎችን በመያዝ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ወንጀል የመከላከል ሥራም ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

ያም ሆኖ በሞተር ሳይክልና በመኪና የሚፈጸሙ ወንጀሎችና የጫኝና አውራጅ የመቆጣጠሩ ሥራ ባለው የሕግ ክፍተት በሚፈለገው ልክ መከላከል አለመቻሉን ጠቅሰዋል።

በተደጋጋሚ የቅሚያና የስርቆት ወንጀል የሚፈጸምባቸው መኪናዎችና ሞተር ሳይክሎች ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈጽመው የወጡ ተሽከርካሪዎች እንዳሉበት ጠቁመዋል።

ለዚህም የወንጀል ድርጊት የሚፈጽሙ ተሽከርካሪዎች ሕጉ ጠበቅ ያለ እርምጃ ስለማይወስድባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በክፍለ ከተማው የወንጀል ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ታሪኩ እንደገለጹት፤  በርካታ ወንጀሎችን በኅብረተሰቡ ተሳትፎ መከላከል ተችሏል።

አንዳንድ ወንጀሎች አሁንም በግለሰቦችና በተቋማት ግዴለሽነት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ጠቁመው ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

በክፍለ ከተማ እየታ ያለው የወንጀል መከላከል ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኅብረተሰቡ የሚያሳየውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም