ሚኒስቴሩ ጉዳት ለደረሰባቸው ተቋማት ከ187 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ ጉዳት ለደረሰባቸው ተቋማት ከ187 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ
ባህር ዳር ሚያዚያ 20/2014 (ኢዜአ) የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ኢንተርፕራይዞች በጥሬ ገንዘብና በአይነት ከ187 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ።
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በባህር ዳር ከተማ በተደረገው የድጋፍ ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በፈፀመው ወረራ በክልሉ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል።
"ይሁን እንጂ የደረሰውን ውድመት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመተባበር መመለስ እንደምንችል አምነን ባቀረብነው ጥሪ መሰረት በርካታ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል" ብለዋል።
መላው ህዝብ በአንድነት ፀንቶ እያደረገ ያለው ትብብርና ድጋፍ የሚያኮራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በዛሬው እለትም የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ያደረገው ድጋፍ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ፈጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትንና ኢንተርፕራይዞችን ለማቋቋም ለተደረገው ድጋፍ ዶክተር ይልቃል ምስጋና አቅርበዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ ባካሄደው ወረራ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ በኢንተርፕራይዞችና አንቀሳቃሾች ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
"የደረሰውን ጉዳት ቀድመን በማስጠናት ተጠሪ ተቋማትን ሁሉንም ክልሎች፣ አቻ መስሪያ ቤቶችንና ረጅ ድርጅቶችን በማስተባበር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገ ነው" ብለዋል ።
ተቋማቱን ለማቋቋም በዛሬው እለት ለኢንተርፕራይዞች የሚውል በጥሬ ገንዘብ 30 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ማሽኖችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ያካተተ የአይነት ድጋፍ መደረጉን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።