ቀጥታ፡

የይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ነገ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ ነሀሴ 2/2010 ከሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በመካኒሳ ዶንቦስኮ ካቶሊክ ትምህርት ቤት ሜዳ ሲካሄድ የቆየው በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው የይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ 13ኛው የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ነገ ይጠናቀቃል። በውድድሩ 80 የአዲስ አበባ ቡድኖችና ስምንት የክልል ቡድኖች በድምሩ 88 ቡድኖች የተሳተፉበት ሲሆን ምንም ዓይነት የውድድር እድል ላላገኙ እድሜያቸው 14 እና 15 ዓመት በሆኑ ታዳጊዎች መካከል እየተካሄደ ያለ ውድድር ነው። ከነሐሴ 12 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ምድቦች ተከፋፍሎ ሲካሄድ የቆየው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ነሐሴ 29 ቀን ቀን 2010 ዓ.ም የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ተደርገው ውድድሩ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ምንሊክ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጳጉሜ 3 ቀን 2010 ዓ.ም የነገ ተስፋ የታዳጊ ቡድንና ድል የታዳጊ ቡድን ከቀኑ 4 ሰአት ላይ የፍጻሜ ጨዋታቸውን ያካሄዳሉ። የነገ ተስፋ በግማሽ ፍጻሜው መካኒሳን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ድል ከአንለያይም 1 ለ 1 ተለያይተው በመለያ ምት ድል 7 ለ 6 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረሳቸውን ተናግረዋል። በግማሽ ፍጻሜው የተሸነፉት አንለያይምና መካኒሳ ለደረጃ ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት ከቀኑ 3 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል። በየዓመቱ የሚካሄደው ውድድር አላማው ተተኪ ተጫዋቾችን በማፍራት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሆነም ነው አቶ ምንሊክ ያስረዱት። በውድድሩ ለመሳተፍ 122 ቡድኖች ከአዲስ አበባና ከክልል ከተሞች የተመዘገቡ ቢሆንም በተደረገው የእድሜ ተገቢነት ማጣራት ትክክለኛውን የእድሜ ገደብ ያሟሉና ብቁ ሆነው የቀረቡት 88 ቡድኖች መመረጣቸውን አስታውሰዋል። በቀደሙት ተመሳሳይ ውድድሮች ምንተስኖት አዳነ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ ኤልያስ ማሞ፣ አህመድ ረሺድ (ሽሪላ)ን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች መገኘታቸውንም ነው አቶ ምንሊክ ያስረዱት። ይድነቃቸው ተሰማ ለአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለ23 ዓመታት ተጫውተው ያሳለፉ ሲሆን፤ በቆይታቸው ዝነኛ ተጫዋች ነበሩ። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ስፖርትን ያስፋፋና ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያደረሱ በኳስ ተጫዋችነት በአሰልጣኝነት በእግር ኳስ አመራር ሰጪነት በመሳተፍ በስፖርቱ ዓለም ምኞታቸውን ማሳካት የቻሉ ታላቅ የስፖርት ሰው ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም