የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጎልበት በተለያዩ መልኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍታት አለብን - ኢዜአ አማርኛ
የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጎልበት በተለያዩ መልኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍታት አለብን
ሚያዝያ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)''የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጎልበት በተለያዩ መልኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍታት አለብን '' ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ 'ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት ጉዞ' ጥሪን ተቀብለው ለመጡ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ የአገረ መንግስት ቁልፍ መገለጫ የሆኑና ህዝብን ያስተሳሰሩ የአብሮነት እሴት ባለቤት መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ብዝሃ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ለበርካታ ዘመናት ተከባብረው በጋራ መኖራቸውንም ለአብነት አንስተዋል፡፡
ነገር ግን አሁን ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ይህን የአብሮነት እሴት የማይመጥኑ ድርጊቶች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቁመው፤ እነዚህ ድርጊቶች ከወዲሁ ሊታረሙ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም የአብሮነትን እሴቶችን በማጎልበት በተለያየ መልኩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር እድሪስ በበኩላቸው እንደ አገር በመመካከርና በመተባበር ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አለብን ነው ያሉት።
በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰላም፣ አንድነትና መተባበርን የዘወትር እሴታቸው አድርገው እንዲሰሩም ነው መልዕክት ያስተላለፉት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው "ዳያስፖራው ኢትዮጵያን በማገዝ ረገድ የጠላትን አንገት የሚያስደፋና ወዳጅን ደግሞ የሚያኮራ ተግባር እየፈጸመ ይገኛል" ብለዋል።
በርካታ ቁጥር ያለው ዳያስፖራ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለአገሩ ያለውን አለኝታነት በተግባር ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡