ቀጥታ፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰቡ

ሚያዚያ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ አሳሰቡ።

1 ሺህ 443ኛውን የኢድ በአልና ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ፤ ያልተረጋገጠ ወሬ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ከሰሞኑ በተከሰተው ግጭት አሳዛኝ ድርጊት መፈጸሙ የሚወገዝ እና የትኛውንም ሃይማኖት የማይወክል እንደሆነ ገልጸዋል።

ለህዝቡ ቅርብ የሆኑና ተሰሚነት ያላቸው አካላት ግጭት አባባሽ መልእክቶችን በማሰራጨት እልቂት እንዲፈጠር እየሠሩ እንደሚገኙ አመልክተው፤ ህዝቡ የተነገረው ሁሉ አምኖ መቀበል ብቻ ሳይሆን መርምሮ ማረጋገጥ እንዳለበት አስረድተዋል።

ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ የፀጥታ አካላት እና የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ሀላፊነታቸውን መወጣት ላይ ክፍተት እንዳሉባቸው ገልፀው፤ ችግሩ ከዚህ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኮሚቴ በማቋቋም እና ቦታው ድረስ በማቅናት ችግሩን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም