ቀጥታ፡

በጎንደር የተከሰተውን ችግር በማባባስ ሰላምን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ማስቆም ይገባል

ሚያዝያ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎንደር የተከሰተውን ችግር በማባባስ ሰላምን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ማስቆም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ ድርጊቱ ከኃይማኖት ውጪ የሆነ፤  የተወገዘ መሆኑን ገልጿል።   

የጉባኤው ጠቅላይ ጸኃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ በተፈጸመው ድርጊት የሰው ሕይወትና ንብረት ውድመት የሰማነው በተሰበረ ልብ ውስጥ ሆነን ነው ብለዋል።     

"ሰው በሰውነቱ ሊከበር ይገባል፤ ሰው በመሆኑ ብቻ የመኖር ዋስትናው ሊረጋገጥ ይገባል" ያሉት ጸኃፊው መንግሥት የዜጎች ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።  

"ጥፋትን በጥፋት መመለስ አይቻልም፤ ይልቁንም ችግሩ እንዲሰፋ የሚያደርግ በመሆኑ ከእንደዚህ ዓይነት እኩይ ተግባር መቆጠብ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል።

ችግሩን በማባበስ የበለጠ ደም መፋሰስ እንዲመጣ የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን በመረዳት የሚመለከተው አካል ሊያስቆመው እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለችግሮች መፍትሄ የሚመጣው በሰከነ መንገድ በውይይት መሆኑንም በመጠቆም።       

እንደ ቀሲስ ታጋይ ገለጻ በግጭቱ ተሳትፈው ለሰው ሕይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት የሆኑ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ ተወስዶ ለኅዝቡ በይፋ ሊገለጽ እንደሚገባ አመልክተዋል።      

የኃይማኖት ተቋማት እንደዚህ ዓይነት ከኃይማኖት አስተምህሮ ያፈነገጠ ነገር ሲከሰት ማስተማርና መመለስ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም