የቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክ ማልማት የሚያስችል የ10 አመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክ ማልማት የሚያስችል የ10 አመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ
ሁመራ ነሀሴ 1/2010 በትግራይ ክልል የሚገኝ የቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክን ለማልማት የሚያስችል የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ ፓርኩን ማልማት በሚቻልበት ዙሪያ የተዘጋጀ የሦስት ቀናት የውይይት መድረክ በሁመራ ከተማ ተካሄደዋል፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለጹት ፍኖተ ካርታው በክልሉ ምእራብና ሰሜን ምእራብ ዞኖች የሚገኘው ቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክን ከአደጋ በመጠበቅ ለቱሪዝም መስህብ ለማዋል ያስችላል፡፡ እንዲሁም ፍኖተ ካርታው ህብረተሰቡን ባለቤት በማድረግ የፓርኩን ደህንነትና ጥበቃ ለማዘመንና በውስጡ የሚገኙ እንስሳት ለማጥናትና ለማስተዋወቅ እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ፓርኩን ለቱሪስት መስህብ አገልግሎት ለማዋል ባለሃብቶች በአቅራቢያው መሰረተ ልማት እንዲያስፋፉ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፖርኩን የመጠበቅ ኃላፊነት የፌደራል ቢሆንም የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለፓርኩ ደህንነት እያደረገ ያለውን ጥበቃና ድጋፍ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክ ዝሆን፣ አጋዜን፣ አነር፣ ሚዳቋ፣ ከርከሮ ፣ ጥርኝ፣ ሌሎች የዱር እንስሳት የሚገኙበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ አረፋይነ በበኩላቸው ፓርኩ በህገ ወጥ አደን፣ በባህላዊ ማአድን ቁፋሮና የእርሻ ስራ ምክንያት ለአደጋ ሲጋለጥ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ ''ፍኖተ ካርታው መጽደቁ ህዝቡን የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው በማድረግ የተሻለ ስራ ለመስራት ይረዳል'' ብለዋል፡፡ ''ቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክ የራሳችን ሃብት ስለሆነ ልንጠብቀው ይገባል'' ያሉት ደግሞ በፓርኩ አቅራቢያ የሚኖሩ አርሶ አደር መረሳ ደረስ ናቸው፡፡ ህብረተሰቡ ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ ደን መቁረጥ፣ እንስሳትን ማደንና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራትን መፈፀም የፖርኩን ህልውና አደጋ ላይ መጣል በመሆኑ ልንከላከል ይገባል ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ምኡዝ ሰሎም ናቸው፡፡ ቃፍታ ሽራሮ ብሄራዊ ፓርክ 2 ሺህ 176 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውና ከ42 በላይ አጥቢ የዱር እንሰሳት ዝርያዎች ፣ ከ163 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎችና ሌሎች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ በአውደ ጥናቱ ከፌደራል፣ ከክልልና ከዞን የተውጣጡ አመራር አካላትና የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በፓርኩ ዙሪያ የተሰሩ አምስት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡