በሐረሪ ክልል “ኢድ አልፈጥር እና ሸዋል ኢድ” በዓላት ላይ የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል “ኢድ አልፈጥር እና ሸዋል ኢድ” በዓላት ላይ የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ሐረር፤ ሚያዝያ 19 /2014 (ኢዜአ) የሐረሪ ክልል ለ“ኢድ አልፈጥር እና ሸዋል ኢድ” በዓላት የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በዓላቱን ለማክበር ወደ ክልሉ የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ በክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የሚመራ ግብረሃይል ተቋቁሞ ወደስራ መገባቱን የጽህፈት ቤት ሃላፊው አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የጽዳትና ውበት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የሐረሪ ክልል የቱሪስት መዳረሻና ምቹ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሄኖክ፤ ለእንግዶች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።
በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሳተፉ ዲያስፖራዎችም የክልሉ መንግሥት መደላድል እንደሚፈጥርም አንስተዋል።
በተለይ በውጭ የሚኖሩ ተወላጆች ወደ ክልሉ መጥተው በዓሉን በጋራና አብሮነት እንዲያሳልፉ በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመላክተዋል።
የኢድ አልፈጥር እና የሸዋል ኢድ በዓላትን በድምቀት ለማክበር ብሎም ለአንግዶቹ ወንድማማችነትን የሚያጎለብት አቀባበል ለማድረግ ከወጣቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ ሄኖክ አስታውቀዋል።