በጎንደር የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት መንግስት በትኩረት ይሰራል- ዶክተር ጌታቸው ጀምበር - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት መንግስት በትኩረት ይሰራል- ዶክተር ጌታቸው ጀምበር
ጎንደር ፤ ሚያዚያ 19/2014(ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር አሰታወቁ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ከጎንደር ከተማ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ከእምነቶቹ ተከታዮች ጋር በተፈጠረው ችግርና መፍትሄው ዙሪያ ውይይት ማካሄድ ጀምረዋል።
በውይይቱ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ እንደገለጹት፤ ትናንት በታላቋ መናገሻ የጎንደር ከተማ የተፈጠረው ችግር ሁሉንም ያሳዘነ ነው።
የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት በመፍታት በኩል የእምነቱ ተከታዮች ብስለት በተሞላበት መንገድ በጋራና በቅንጅት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ጎንደር ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነትና በመከባበር የሚኖሩባት ታላቅ ከተማ መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህንኑ የተሰናሰለ የአኗኗር ስልት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ግጭቱ እንዲፈጠር ያዳረጉ አካላት ላይ አስፈላጊውን ማጠራት በማድረግ ጥፋተኞችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ስራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡ የመንስኤው አካል በመሆን ከመንግስት ጋር እንዲሰራ አሳስበዋል።