ቀጥታ፡

ኢትዮ-ቴሌኮም ሁለት አዳዲስ አገልግሎቶችን ይፋ አደረገ

ሚያዝያ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ)ኢትዮ-ቴሌኮም 'አሻም ቴሌ' እና 'ቴሌ ገበያ' የተሰኙ አዳዲስ አገልግሎቶችን ይፋ ማድረጉን አስታወቀ።

የተቋሙ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በተገኙበት አገልግሎቶቹን ይፋ ማድረጊያ መርሃ-ግብር ተከናውኗል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አዳዲስ አገልግሎቶቹ ደንበኞች ከኩባንያው ጋር ያላቸውን ትስስር የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።

አገልግሎቶቹም ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሆኑ ገልጸዋል።ከአገልግሎቶቹ አንዱ የሆነው 'አሻም ቴሌ' ደንበኞች የኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎትን ሲያገኙ በሚሰበሰብላቸው ነጥብ መልሶ የሚከፍል የአገልግሎት አይነት ነው ብለዋል።

ደንበኞች የቴሌኮም አገልግሎት ሲጠቀሙ እንዲሁም ክፍያቸውን በቴሌ ብር ሲፈጽሙ በሚሰበስቧቸው ነጥቦች አማካኝነት ሽልማት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

ይህ ማለት ደንበኞች አገልግሎት ለማግኘት በሚፈጽሙት የአገልግሎት ግዢ ብዛትና በቴሌ ብር በተፈጸመ ክፍያ ብዛት የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረጊያ ስልት መሆኑንም አክለዋል።በዚህም መሰረት በ'አሻም ቴሌ' የሚመዘገቡ ደንበኞች በሚያስመዘግቡት ነጥብ መጠን ማበረታቻ እንዲያገኙ ይረዳል ብለዋል።

ሌላው ይፋ የሆነው አገልግሎት 'ቴሌ ገበያ' ሲሆን ይህ ደግሞ የቴሌኮም አገልግሎት 'ኦን ላይን' ሽያጭ አማካኝነት ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረጊያ ነው ብለዋል።

በዚህም ካሉት ከ600 በላይ የሽያጭ ማዕከላት በተጨማሪ ደንበኞች ካሉበት ሆነው የኢትዮ-ቴሌኮም ምርቶችን በቴሌ ብር አማካኝነት መግዛት እንዲችሉ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ደንበኞች የሞባይል ቀፎዎችን፣የኢንተርኔት መጠቀሚያ ሞደሞችን፣ መደበኛ ብሮድ ባንድ ኢንተርኔት እና ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ደንበኞች 'ቴሌ ገበያ' የኢትዮ-ቴሌኮም ድረ-ገጽን በመጠቀም የሽያጭ ማዕከላትን ማግኘት እንደሚችሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም