የሃይማኖቶች የአብሮነት እሴቶችን ለመናድ የሚሯሯጡ ሃይሎችን ማስቆም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖቶች የአብሮነት እሴቶችን ለመናድ የሚሯሯጡ ሃይሎችን ማስቆም ይገባል
ጎንደር፤ ሚያዚያ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዘመናት የተሻገረውን የሃይማኖቶች የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶችን ለመናድ የሚሯሯጡ ቡድኖችን ሁሉም የሃይማኖት ተከታዮች በጋራ ሊታገሉዋቸው ይገባል ሲሉ የጎንደር ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት አሳሰቡ፡፡
የሃይማኖት ተቋማቱ ጉባኤ አባላት በሃይማኖት ሽፋን በጥፋት ቡድኖች የተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት የትኛውንም እምነት የማይወክሉ በመሆኑ አጥብቀው እንደሚወግዙት አስታውቀዋል።
የጉባኤው አባላት በሰጡት መግለጫ በጎንደር ከተማ በኦርቶዶክስና በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መካከል የተፈጠረው ግጭት የእምነት ተቋማቱን የማይወክል የጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች የጥፋት ተልዕኮ መሆኑን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ አባ ዮሴፍ ደስታ እንዳሉት ሰላምን የማይሹ ኃይሎች አሁንም በሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለማስነሳት እየሞከሩ ነው።
ሁለቱ ሃይማኖቶች ዘመናት የተሻገረ የአብሮነትና የመቻቻል ሃይማኖታዊ እሴቶች የገነቡ የእምነት ተቋማት መሆናቸውን በመግለጫቸው አመልክተዋል።እነዚህን እሴቶች ለመናድ የሚሹ ኃይሎችን ድብቅ ዓላማ በመረዳት የእምነቱ ተከታዮች በጋራ መታገል እንዳለባቸው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ስለሰላምና የሃይማኖት እኩልነት መሰረታዊ አስተምህሮ ያላት እንደመሆኗ ዛሬም ለሰላምና ለሰው ልጆች ክብር ታላቅ ቦታ በመስጠት አበክራ ትሰራለች ሲሉ አባ ዮሴፍ አረጋግጠዋል።
''በጎንደር ከተማ ትናንት የተፈጠረው ግጭት የሁለቱን ሃይማኖቶች ክብርና ልዕልና የማይመጥን ነው'' ያሉት አባ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያኗ ችግሩ በሰላምና በውይይት እንዲፈታ አስፈላጊውን ጥረት እንደምታደርግም አስታውቀዋል፡፡
የሰው ልጅ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለማራመድ የሚችለው ሰላም ሲኖር ብቻ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ ለዘላቂ ሰላም መስፈን አጥብቃ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
የጎንደር ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት አገልጋይ አማን ሷልህ በበኩላቸው ግጭቱ እንዲፈጠር ያደረጉ ቡድኖች የሃይማኖት ካባ የለብሰው ነገር ግን የእምነቱ ተከታዮች ያልሆኑ አካላት ናቸው።
በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ግጭትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ያደረጉ ቡድኖች በእምነት ሽፋን ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ የሚሯሯጡ መሆናቸውን በአፅዕኖት ተናግረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው በሃይማኖቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ የሰው ህይወት እንዲጠፋ እና ንብረት እንዲወድም ያደረጉ የጥፋት ቡድኖችን መንግሥት በአስቸኳይ አጣርቶ ለህግ እንዲያቀርብ ጥሪ ያቀርባል ብለዋል።
የሁለቱ እምነት ተከታዮችና የእምነት አባቶች ለሰላም ልዩ ትኩረት በመስጠት ሃይማኖታዊ የአብሮነት እሴቶቻችን እንደ ቀደመው ሁሉ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ በጋራ ተቀራርበው እንዲሰሩም አሳስበዋል።
የሃይማኖት ተቋማቱ ጉባኤ አባላቱ በመግለጫቸው በሃይማኖት ሽፋን በከተማው ብጥብጥና ግጭት እንዲፈጠር ያደረጉ ቡድኖች እምነቱን የማይወክሉ የጥፋት ተልዕኮ አራማጆች በመሆናቸው አጥብቀን እናወግዛለን ብለዋል።