ከ2 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ 74 ተሽከርካሪዎች መቀሌ ገቡ

44

ሚያዚያ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከ2 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ 74 ከባድ ተሽከርካሪዎች ዛሬ መቀሌ መግባታቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለትግራይ ክልል የሚያስፈልገውን የእርዳታ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ እንዳስታወቀው፤ አቅርቦቱ መቀሌ በሚገኘው የድርጅቱ መጋዘን በመራገፍ ላይ ይገኛል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የአጋር ድርጅቶች የካርጎ ጫኝ ተሽከርካሪና የነዳጅ ቦቴዎች መቀሌ መግባታቸውን ገልጿል።

74 ከባድ ተሽከርካሪዎች የሰብዓዊ ድጋፍ በመጫን ከሰመራ ከተማ ተነስተው ወደ መቀሌ ማምራት እንደጀመሩ የኢትዮጵያ መንግስት መግለጹ ይታወቃል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የዛሬውን ሳይጨምር ከእ.አ.አ 2021 ታህሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ በሁለት ዙር 2 ሺህ 350 ሜትሪክ ቶን የሰብአዊ እርዳታና 162 ሺህ ሊትር ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል ማስገባቱን ኢዜአ ከድርጅቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ድርጅቱ ከእ.አ.አ 2021 መግቢያ አንስቶ በአፋር፣ ትግራይና አማራ ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ወገኖች የሕይወት አድን የምግብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም