የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር ለሶማሌ ክልል ድርቅ ተጎጂዎች ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የምግብ ድጋፍ አደረገ

79

ሚያዝያ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር ለሶማሌ ክልል ድርቅ ተጎጂዎች ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የምግብ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ለሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ትናንት ማምሻውን በጂግጅጋ በተዘጋጀ የኢፍጣር ሥነ-ሥርዓት ላይ አስረክበዋል።

በርክክቡ ወቅት ኢንጂነር አይሻ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር በድርቅ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ዜጎችን ለመደገፍ በ300 ሚሊዮን ብር ውሃና የእንስሳት መኖ ሲያቀርብ ቆይቷል።

የአሁኑ ድጋፍ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር በድርቁ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለመታደግ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ከክልሉ ጋር በመሆንም በድርቁ የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋምና ዘላቂ የምግብ ዋስትና እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ስራዎች ለመተግበር ሚኒስቴሩ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የሶማሌ ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በበኩላቸው፤ ለድርቅ ተጎጂ ወገኖች የሚኒስቴሩ ድጋፍ በወሳኝ ወቅት የተደረገ የእርስ በርስ መረዳዳት ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል።

ከድጋፉም ውስጥ የዕለት ፍጆታ የመግዛት አቅም ለሌላቸው 400 ቤተሰቦች የሚያገለግል ምግብ እንደሚገኝበት ተናግረዋል።

“በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ዝናብ እየጣለ ቢሆንም በሁሉም ወረዳዎች ባለመዳረሱ የእርዳታ ፈላጊው ህዝብ በርካታ ነው፤ የተደረገው ድጋፍ ለአስቿካይ የምግብ እርዳታ ግዥ በማዋል ለድርቅ ምላሽ እንጠቀምበታለን” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም