ቀጥታ፡

በባሌ ዞን ተጨማሪ 70 ሺህ ልጆችን ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጎባ ጳጉሜ 1/2010 በባሌ ዞን በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 70 ሺህ  ልጆችን በተጨማሪ በመቀበል ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጎሳ ግዛው ለኢዜአ እንዳሉት በ2011 የትምህርት ዘመን  494 ሺህ 960 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ለመቀበል ታቅዶ ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ እስካሁንም በእቅድ ከተያዘው ውስጥ በቤት ለቤት ምዝገባ ጭምር  40 በመቶው  ተከናውኗል፡፡ የተቀሩትን ተማሪዎች በመደበኛው የምዝገባ መርሓ ግብር ወቅትና በየወረዳው በተቋቋሙ ግብረ ኃይል አማካኝነት ለመመዝገብ  እየተሰራ ነው፡፡ ኃላፊው እንዳሉት ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ከታቀደው ውስጥ  70 ሺህ ያህል እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን በተጨማሪ ለመቀበል  ነው ዝግጅት እየተደረገ ያለው፡፡ ከዝግጅቱም መካከል ወደ ትምህርት ገበታ ለሚመጡ ተማሪዎች ምቹ የስራ አካባቢ ለመፍጠር 126  ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣ የትምህርት ቤቶች ጥገናና የተማሪዎች መቀመጫ ግዥ በህብረተሰቡ ተሳትፎና በመንግስት ድጋፍ መከናወናቸው ይገኙበታል፡፡ " የተገነቡት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች የተማሪ ክፍል ጥምርታን በማስተካከል ለትምህርት ጥራት የጎላ ድርሻ ይኖራቸዋል" ብሏል፡፡ በዞኑ ጋሰራ ወረዳ የተማሪ ወላጆች መካከል የጋሰራ ናቄ ነጋዎ ቀበሌ ነዋሪ  አቶ አሰፋ ድርባ በሰጡት አስተያየት " ከዚህ በፊት ሁለት ልጆቼን  እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በማስተማር ለወግ አብቅቻለሁ" ብሏል፡፡ አሁንም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ የቀበሌያቸው ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ከአካባቢያቸው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር የቤት ለቤት ትምህርት ሲሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ወደ ትምህርት የሚመጡ ተማሪዎች በክፍል ጥበት ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ በክረምቱ ወራት የአካባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበር ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች በትምህርት ቤታቸው መሰራታቸውን የተናገሩት ደግሞ የደምበል ቀበሌ ነዋሪ አቶ አህመድ ሙስጠፋ ናቸው፡፡ ባለፈው የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤታቸው ብዛት ያላቸው ተማሪዎች በአንድ ክፍል ተጣበው  ሲማሩ መቆየታቸውን የተናገረው ደግሞ የዋሪዮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ቢላል ሙክታር ነው፡፡ በቅርቡ ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን የሚያገለግሉ  አዳዲስ ተጨማሪ ክፍሎች መሰራታቸውንና  ይህም የነበረውን የክፍል ጥበት ችግር እንደሚያቃለል ገልጿል፡፡ በባሌ  ዞን በ2011  የትምህርት ዘመን 817 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም