በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራው ልዑካን ቡድን ከቢል እና ሜሊናዳ ጌትስ የጋራ መስራችና ሊቀመንበር ሜሌንዳ ጌትስ ጋር ውይይት አደረገ

168

ሚያዝያ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራው ልዑካን ቡድን ከቢል እና ሜሊናዳ ጌትስ የጋራ መስራችና ሊቀመንበር ሜሌንዳ ጌትስ ጋር ውይይት አደረገ።

ልዑካን ቡድኑ ውይይቱን ያደረገው በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ከሚገኘው የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) የፀደይ ወቅት ስብስባ ጎን ለጎን መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ውይይቱ ቢል እና ሜሊናዳ ጌትስ በኢትዮጵያ በጤና፣ግብርናና ዲጂታል ዘርፎች እያደረገ ባለው ድጋፍ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በያዝነው ሳምንት ከቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የዓለም አቀፍ ልማት ፕሮግራም ፕሬዝዳንት ክርስቶፍ ኤሊያስ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ኘሮግራሞችን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እ.አ.አ በ2000 የተቋቋመ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት ነው።

በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራው ልዑካን ቡድን የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) የፀደይ ወቅት ስብስባ በመሳተፍ ላይ ነው።

ልዑካን ቡድኑ ከስብሰባው ጎን ለጎን የሁለትዮሽና የባለብዙ መድረክ ምክክሮች በማድረግ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ቡድኑ ከቀናት በፊት ከብሪታኒያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ጋር በሁለትዮሽና የኢኮኖሚ ትብብር ጉዳዮች ውይይት ማድረጉ ይታወሳል።

ላለፉት ስድስት ቀናት በዋሺንግተን ዲሲ ሲካሄድ የነበረው የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) የፀደይ ወቅት ስብስባ ትናንት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም