በኢትዮጵያ ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ትምህርት ቤት እንዲገቡ የትምህርት አመራሮች ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ትምህርት ቤት እንዲገቡ የትምህርት አመራሮች ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው
አዲስ አበባ ጶግሜ 1/2010 በኢትዮጵያ ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ትምህርት ቤት እንዲገቡ በየደረጃው ያሉ የትምህርት አመራሮች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ። ኢትዮጵያ በመደበኛና ቅድመ መደበኛ ትምህርት ከ 28 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የትምህርት እድል ተጠቃሚ ማድረግ ቢቻልም በትምህርት ገበታ ላይ መገኘት ካለባቸው ህፃናት አንጻር ግን ቁጥር ዝቅተኛ ነው ተብሏል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 27ኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ "ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በአዲስ መንፈስ እንሰራለን" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ እየተካሄደ ነው። የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይ አቶ ብርሃኑ ሞረዳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት መንግስት ከፍትኛ ጥረት ቢያደርግም ከትምህርት ገበታ ውጭ ያሉ ህጻናት አሁንም ብዙ ናቸው። ከ 2005 እስከ 2009 ዓ.ም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተሳትፎ ከ 47 በመቶ ቢደርስም በአገሪቱ መማር ከሚገባቸው ህፃናት ቁጥር አንፃር ቁጥሩ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል ከ 5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ጥቅል ተሳትፎ 59 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን ለማሳካት ካቀደችው 95 በመቶ አንፃር ሲታይ 20 በመቶ ህፃናት ከትምህርት ቤት ውጭ መሆናቸውን ገለጽዋል። ይኸውም በቀጣይ አገሪቱን የሚረከቡ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንቅፋት በመሆኑ የትምህርት አመራሩ በሃላፊነት ስሜት ስራውን ማከናወን ይጠበቅበታል ብለዋል። የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት፣ የትምህርት አመራሮች ቁርጠኝነት ማነስ፣ የትምህርት ቤቶች ሀፃናትን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም ውስንነቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። በመሆኑም የትምህርት አመራሩ የተጠያቂነት አሰራር ስርዓት በመዘርጋት አቅደውና ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ታቦር ገብረመድህን በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ መማር በሚገባቸው እድሜ ወደ ትምህርት ቤት ያልገቡ በርካታ ህፃናት እንዳሉ ጠቁመዋል። በከተማዋ በትምህርት ገበታ ላይ የማይገኙ ህፃናት እንዳይኖሩ የአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም ነባር ትምህርት ቤቶችን አፍርሶ በማደስና በማስፋፋት፣ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የትምህርት ቤቶችን የቅበላ አቅም ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። የትምህርት ግብዓት በማሟላት፣ ቴክኖሎጂዎችን ማቀረብ፣ ማህበረሰቡን በትምህርት ስራ ማሳተፍ፣ የትምህርት አመራሩንና መምህራንን አቅም ማጎልበት ላይ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የትምህርት ስልጠና ችግሮችን ለመፍታት የቀረበውን የትምህርት ፍኖተ ካርታ በአግባቡ በመፈተሽ ገንቢ አስተያየት በመስጠት ለውጤታማነቱ መትጋት ይገባልም ብለዋል።