ማህበሩ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ800ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ800ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ሻሸመኔ ሚያዝያ 15/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ምዕራብ አርሲ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በፀጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ800ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉ የተደረገው በጸጥታ ችግር ለተፈናቀሉ ሁሩ ባሮ፣ ገመቹና ሃራ ቁኑዲ ቀበሌ ነዎሪዎች መሆኑ ተነግሯል ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ከማል አብደላ ለኢዜአ እንደገለጹት 2ሺህ 624 ቤተሰብ ላላቸው ለ74 አባወራዎች የምግብ፣ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ መገልገያና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ያካተተ ድጋፍ ተደርጓል።
የምዕራብ አርሲ ዞን ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከማል ኢብራሂም ቅርንጫፉ ለተፈናቃይ ወገኖች ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ የመንግስት ተቋማት፣ ባለ ሃብቶችና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካካል የገመቹ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገመዳ ጃሮ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።
ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ዘላቂ ሰላም ተፈጥሮ ወደ ነበሩበት መመለስ እንዲችሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ በወረዳው ሁሮባሮ ቀበሌ ነዋሪ ጃሮ በሹሮ በበኩላቸው መንግስት ዘላቂ መፍትሔ ሊፈጥርላቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።