የትንሣኤ በዓልን በጎ ተግባራት በመፈጸም ማክበር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የትንሣኤ በዓልን በጎ ተግባራት በመፈጸም ማክበር ይገባል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 15/2014 /ኢዜአ/ የትንሳኤ በዓልን በጎ ተግባራት በመፈጸም ማክበር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።
ጉባኤው ለኢዜአ በላከው መግለጫ ለመላው የክስርትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳቹ መልዕክት አስተላልፏል።
በመግለጫው የትንሳኤ በዓል በክርስትና ኃይማኖት ከሚከበሩ ዓበይት በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሷል።
በዓሉ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ርህራሄንና በጎነትን የሚያስተምር መሆኑንም ገልጿል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መድህን በመሆን ሰዎች መልካም ይሆኑ ዘንድ ያስተማረበት እንደሆነም አስታውሷል።
በመሆኑም በዓሉን ለሰው ልጆች ፍቅርን፣ ርህራሄና ሰብዓዊነትን በመስጠት ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤው አስገንዝቧል።
አሁን ላይ በአገሪቱ እየታየ ያለውን አለመግባባትና ግጭት እንዲወገድ በኃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት መንቀሳቀስ እንደሚገባም አሳስቧል።
ሰላምን፣ መከባበርን፣ ፍቅርን፣ አንድነትና ሰብዓዊ ወንድማማችነትን ማጠናከር እንደሚገባም እንዲሁ።
በተለያዩ ምክንያት ተጎጂ የሆኑና ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙትንና የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት እንደሚገባም ገልጿል።
በየህክምና ተቋማቱ የሚገኙ ህሙማንና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያንን በማገዝም በጎ ምግባር በመፈጸም ኃይማኖታዊና ወገናዊ ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ ጉባኤው አሳስቧል።