ቀጥታ፡

የትንሳኤ በዓልን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ማሳለፍ ይገባል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 15/2014 /ኢዜአ/ ኅዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

በነገው ዕለት የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሳኤን በማስመልከት የኃይማኖት አባቶች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትሪያሪክ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ እንደተናገሩት፤ ትንሳኤ ክርስቶስ ለክርስትያኖች ምድራዊ ህይወትም ሆነ ሰማያዊ ህይወት የላቀ ትርጉም ያለው ነው።

ትንሳኤው በምድራዊ ህይወት ከግብረ ኃጢአት በመራቅ፣ በበጎ ሥራ፣ ፍቅርና አንድነት፣ በመተዛዘንና በመተሳሰብ በሰላም ለመኖርና የሞራል ትንሳኤ እንዲኖር የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የክርስቶስ ትንሳኤ ጥላቻንና መጠፋፋትን ያስወገደ፣ ሰላምን ያሰፈነና ዕርቅን ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በዓለ ትንሳኤውን ስናከብር ከእኛ የሚጠበቀውን ዓይነት ክርስቶሳዊ ሕይወት በመላበስ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

በዓሉን በመተሳሰብ በልዩ ልዩ ምክንያት መከራ ላይ የሚገኙ ወገኖችን በማሰብና በመርዳት መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የሰላም፣ የፍቅር፣ የዕርቅና የይቅርታ ኃይሎችንም በመላበስ አገሪቱንና ኅዝቦቿን ከፈተና መታደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በበኩላቸው፤ ትንሳኤውን ከጥላቻ፣ ከመለያየት፣ ከትእቢትና ከክፋት መንፈስ በመራቅ ማሰብ ይገባል።

ሁሉም በሚችለው አቅም ሁሉ ችግረኞችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ ህመምተኞችን፣ ስደተኞችን በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብና በመርዳት ማሳለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርትሲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀንበሩ፤ የትንሳኤው መገለጫ ፍቅር በመሆኑ በዓሉን በፍቅርና በመተሳሰብ ማሳለፍ ይገባል ብለዋል።

በዓሉን ተርበውና ተጠምተው ለተጨነቁ ወገኖችን እንዲሁም በሰላም እጦት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ተስፋቸው ለጨለመባቸው ወገኖችም ያለንን በማካፈል ማሳለፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

እንደ አገር ከጥላቻና ከክፋት በመራቅ በመደማመጥና በመከባበር ችግሮችን በውይይት በጋራ በመፍታት በወንድማማችነት መንፈስ አስተማማኝ ሰላም መገንባት እንደሚገባም የኃይማኖት አባቶቹ አስገንዝበዋል።

የ2014 ዓ.ም የትንሳኤ በዓል በመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በነገው እለት ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም