የ'ሸዋል ኢድ' በዓልን መቻቻል እና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ማክበር ይገባል

ሐረር፤ ሚያዚያ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የ'ሸዋል ኢድ' በዓልን መቻቻል እና የህዝቦችን አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ማክበር እንደሚገባ ተገለጸ። 

ለበዓሉ ዝግጅት ባለፉት 14 ቀናት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን የክልሉ መስተዳደር  ምክር ቤት  ዛሬ በገመገመበት ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፤  በዓሉ የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ ነው።

በመሆኑም የ'ሸዋል ኢድ' በዓል በብሔረሶቦችና በእምነቶች መካከል ያለውን አንድነትና መቻቻል ሊያጠናከር በሚችል መልኩ ሊከበር ይገባል ብለዋል።

በዓሉን ለማክበር በሚደረገው ዝግጅት ማህበረሰቡን በማሳተፍ በዓሉን ህዝባዊ ማድረግ ብሎም እንግዶችን ሐረር በምትታወቅበት የእንግዳ ተቀባይነት እሴት ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዓሉ በከተማ እና ገጠር ብሎም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ  የሚመጡ እንግዶች የሚታደሙበት በመሆኑ  ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ በመቀናጀት መሰራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የከተማ ውበትና ፅዳት ስራውን ብሎም ሐረር ያላትን የዘመናት ታሪክ በሚመጥን መልኩ ለቅድመ ዝግጅቱ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

በዓሉ የልማት ስራዎችን የሚያፋጥንና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ በመሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራው ከወዲሁ እንዲጠናቀቅም የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ዝግጅቱን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት በዓሉን ማክበሪያና እንግዶችን መቀበያ ስፍራ መለየቱን ገልጸዋል።

እድሳት የሚያስፈልጋቸውን ታሪካዊ ስፍራዎች የማደስ ስራ እየተካሄደ  መሆኑን ጠቁመው፤ በሐረር የእንግዳ ተቀባይነት እሴቶችና አብሮነትን የሚያጎለብቱ መድረኮች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

ለእንግዶች ወንድማማችነትን የሚያጎለብት አቀባበል ለማድረግ ወጣቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን ያሳተፈ ዝግጅት መደረጉንም አቶ ተወላዳ አስረድተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከመስተዳድሩ  ምክር ቤት  አባላት ጋር በመሆነ ለበዓሉ  ማክበሪያ እየተዘጋጁ የሚገኙ ስፋራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በሐረሪ ማህበረሰብ ዘንድ  ትልቅ ሥፍራ ያለው ሸዋል ኢድ በየዓመቱ የኢድ አልፊጥር በዓል በተከበረ በሳምንቱ የሚከበር ሲሆን፤ በበዓሉ መላው ዓለም የሚኖሩ ሐረሪዎች፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ቱሪስቶች በብዛት ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም