በጋምቤላ ክልል የትንሳኤ በዓል በሰላም እንዲያከበር ዝግጅት ማድረጉን ፖሊስ ገለጸ

111

ጋምቤላ፤ ሚያዝያ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የትንሳኤ ዓልን ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት እንዲያከብር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ አስታወቁ።

በክልሉ ወንጀልን ለመከላከል የተጠናከረ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ አመልክተዋል።

ኮሚሽነሩ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉ በሰላም እንዲያከብር አስፈላጊው የጸጥታ ኃይል ስምሪት ተደርጓል።

በተለይም በጋምቤላ ከተማና አካባቢው የስርቆትና የዘረፋ ወንጀሎች በሚፈጸምባቸው የስጋት ቀጠናዎች የክልልና የፌዴራል ፖሊስ ጥምር ኃይል መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በተለይም በጋምቤላ ከተማና አካባቢው በሕዝባዊ ውይይት መድረኮች እንደ ችግር የተነሱበትን የስርቆትና የዘረፋ ወንጀሎች ለመቀነስ የ90 ቀናት እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም እየተከናወኑት ባሉ ወንጀልን የመከላከል ስራዎች በጋምቤላ ከተማና አካባቢው በስርቆትና በዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው ብለዋል።

ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ወንጀልን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ሁሉን አቅፍ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር አቡላ አስታውቀዋል።

የክልሉ ነዋሪዎች ለፀጥታ ስጋት የሚሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው ፈጥነው ለፖሊስ እንዲጠቁሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም