የቼስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ በ43ኛው የቼስ ኦሎምፒያድ እንድትሳተፍ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የቼስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ በ43ኛው የቼስ ኦሎምፒያድ እንድትሳተፍ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ ጳጉሜን 1/2010 የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ በ43ኛው የቼስ ኦሎምፒያድ እንድትሳተፍ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ከመስከረም 13 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በጆርጂያ ባቱሚ ከተማ በሚካሄደው የቼስ ኦሎምፒያድ በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያን የሚወክሉ የቡድን አባላትን ለመምረጥ የተዘጋጀው የግል የበላይነት ሻምፒዮና ከሐምሌ 10 እስከ 14 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተካሄዷል። በዚሁ መሰረት በሴቶች ልደት አባተ፣ ፌቨን ገብረመስቀል፣ ሩት ለይኩን፣ መርሃዊት ብርሃነና አስቴር መላክ፤ በወንዶች ብርሃኔ ገብረሚካኤል፣ ግሩም ተክለወልድ፣ ሐፍቶም ገብረመድህን፣ አቤል ማቲዎስና አይዳኙም ግዛቸው ተመርጠዋል። የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ በአጠቃላይ በቼስ ኦሎምፒያድ የሚሳተፉ አባላትን ስም ዝርዝር ለዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን የመላክ ስራ መከናወኑን ለኢዜአ ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቡድኑን የሚወክሉ ተጫዋቾችን የመምረጥ ተግባር ቢያከናውንም በቀጣይ ለሚከናወኑ ስራዎች የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ብሔራዊ ቡድኑ በቼስ ኦሎምፒያዱ እንዲሳተፍ ፌዴሬሽኑ ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ገቢ ለማግኘት ጥረት እያደረገ መሆኑንና ከስፖንሰሮችም ተስፋ ሰጪ ምላሾችን እያገኘ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም የተወዳዳሪዎችና የቡድን መሪ የአውሮፕላን ትኬት ወጪያቸውን ለመሸፈን የስፖንሰር ድጋፍ ለማግኘት መቃረቡንም አመልክተዋል። የበጀት ችግር በመኖሩ ምክንያት ተወዳዳሪዎችን ሆቴል ሰብስቦ ዝግጅት እንዲያደርጉ ባለመቻሉ በግላቸው ዝግጅት ለማድረግ መገደዳቸውንም ጠቅሰዋል። ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግለት ፌዴሬሽኑ በደብዳቤ ከማሳወቁ በተጨማሪ ስለ ውድድሩ አጠቃላይ ይዘትና የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን የያዘ ሰነድ ለሁለቱ ተቋማት በማስገባት ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝም ነው አቶ ሰይፈ የገለጹት። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ናስር ለገሰ የቼስ ፌዴሬሽኑ ለሚኒስቴሩ ጥያቄውን እንዳቀረበ ገልጸው የቀረበው ጥያቄ የውድድሩ ሙሉ ወጪ ይሸፈን የሚል በመሆኑ በበጀት መመሪያው መሰረት ይህን ማድረግ እንደማይቻል ጠቅሰዋል። መመሪያው ሚኒስቴሩ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት በየዓመቱ ላቀዷቸው የውድድርና ስራ ማስኬጃ የበጀት ድጎማ እንደሚደረግና ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ሲኖሩ ራሳቸው ፌዴሬሽኖች ስፖንሰር በማፈላለግ የራሳቸውን ገቢ ማመንጨት እንዳለባቸው ያስቀምጣል ብለዋል። በዚሁ መሰረት ሚኒስቴሩ ለቼስ ፌዴሬሽን ድጋፍ ማድረግ የሚችለው ለውድድሩ የሚያስፈልገውን አብዛኛውን ወጪ በራሱ ሸፍኖ የተወሰነ ድጋፍ ቢጠየቅ የበጀት ድጋፍ ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል። 29ኙም የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት የሚተዳደሩት በዚሁ መመሪያ እንደሆነና የቼስ ፌዴሬሽኑ ከዚሁ አሰራር ውጪ ሊሆን እንደማይችል ነው አቶ ናስር ያስረዱት። በስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት ማቋቋሚያ ደንብ መሰረት አንድ ፌዴሬሽን ወይም ማህበር ሲመሰረት ስፖርቱን በራሱ አቅም ለማስተዳደር ሃላፊነት ወስደው እንደሆነም አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ ታምራት በቀለ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ እንዲደረግለት ጥያቄ ማቅረቡን ገልጸው ነገር ግን የበጀት ውስንነት በመኖሩ ምክንያት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፖርቶች ኦሎምፒክ ወክላ ስትሳተፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ሙሉ ወጪ እንደሚሸፍን ገልጸው አሁን ባለው ሁኔታ ግን ባለው የአቅም ውስንነት ምክንያት ለጥያቄው መልስ መስጠት አልተቻለም ብለዋል። ያም ቢሆን ቼስ ፌዴሬሽኑ ለተወዳዳሪዎቹ እንዲሟላላቸው ያቀረበው የትጥቅ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ድጋፍ እንደሚደረግለት አመልክተዋል። በኦሎምፒክ ኮሚቴው የድጋፍ መመሪያ መሰረት ኢትዮጵያ በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ስትሳተፍ ሙሉ ወጪ እንደሚሸፈንና የዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲሆኑ ግን በሚያስመዘግቡት ውጤት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ስፖርቶች ድጋፍ የሚደረግበት አሰራር እንዳላም አስረድተዋል። ኢትዮጵያ እና የቼስ ስፖርት የረጅም ዓመት ቁርኝት እንዳላቸው ይነገራል። ቼስ ስፖርት ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት «ሰንጠረዥ» በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ውስጥ ይዘወተር እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ።