ቀጥታ፡

ጸሎተ ሐሙስ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በልደታ ማርያም ካቴድራል ተከበረ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2014(ኢዜአ) ጸሎተ ሐሙስ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በልደታ ማርያም ካቴድራል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ተከብሯል፡፡

መርሃ-ግብሩም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌልን ጨምሮ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በልደታ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተከብሯል፡፡

እለቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትህትናን ያስተማረበት ሲሆን፤ በዚህም የቤተ ክርስቲያኗ ሊቀጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል የካህናትንና የምዕመናንን እግር በማጠብ እለቱን አስበዋል፡፡

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በዚሁ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ የሐዋሪያቱን እግር በማጠብ ትህትናውን እንዳስተማረን ምእመኑ ይህንኑ ምግባር በመከተል እርስበርስ መከባበር አለበት  ብለዋል፡፡

በዓሉ ሲከበርም ሆነ በእለት ተለት ኑሮ ለሰዎች በጎ መሆን እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የቤተክርስቲያኗ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዳይሬክተር አባ ተስፋዬ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ "ጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትህትናውንና አክብሮቱን ያሳየበትና ምስጢረ ቁርባንን የገለጸበት በመሆኑ እለቱ ለክርስቲያኖች የተለየ ነው" ብለዋል፡፡

እለቱን ስናከብር ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን እንዲሁ ራሳችንን ዝቅ አድርገን በትህትና ሌሎችን ማገልገል ይገባል ነው ያሉት፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የቤተክርስቲያኗ ምዕመናንም ጸሎተ ሐሙስ ምዕመኑ ትህትናን በመላበስ አንዱ ሌላውን እንዲያገለግል ኢየሱስ ክርስቶስ አርአያ በመሆን ያስተማረበት እለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም